መሳፍንት 4
4
ዲቦራ
1ናዖድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ። 2ስለዚህም እግዚአብሔር በአሦር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነዓን ንጉሥ ለኢያቢስ አሳልፎ ሸጣቸው። የኢያቢስ ሰራዊት አዛዥ፣ በአሪሶት ሐጎይም የሚኖረው ሲሣራ ነበረ፤ 3እርሱም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩት እስራኤላውያንን ሃያ ዓመት እጅግ አስጨነቃቸው፤ እነርሱም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
4በዚያ ጊዜ የለፊዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ በእስራኤል ላይ ፈራጅ#4፥4 በትውፊት መሳፍንት ማለት ነው ነበረች። 5እርሷም በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፣ በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እርሷ ይመጡ ነበር። 6ዲቦራ፣ በንፍታሌም ውስጥ ቃዴስ በተባለች ከተማ ይኖር የነበረውን የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ያዝሃል፤ ‘ተነሣ፤ ከንፍታሌምና ከዛብሎን ዐሥር ሺሕ ሰዎች ይዘህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፤ 7እኔም የኢያቢስን ሰራዊት አዛዥ ሲሣራን ከሠረገሎቹና ከሰራዊቱ ጋራ ቂሶን ወንዝ እንዲመጣ አነሣሣዋለሁ፤ በእጅህም አሳልፌ እሰጥሃለሁ።’ ”
8ባርቅም፣ “ዐብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ፤ ዐብረሽኝ የማትሄጂ ከሆነ ግን አልሄድም” አላት።
9ዲቦራ መልሳ፣ “ይሁን ዕሺ፤ መሄዱን ዐብሬህ#4፥9 ወይም፣ ነገር ግን ልትሄድ ወደ ዐቀድክበት ስፍራ እሄዳለሁ፤ በዚህ ሁኔታ የምትሄድ ከሆነ ግን ክብሩ ለአንተ አይሆንም፤ እግዚአብሔር ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ይሰጣልና” አለችው። ስለዚህ ዲቦራ ከባርቅ ጋራ ወደ ቃዴስ ሄደች፤ 10በዚያም ባርቅ የዛብሎንንና የንፍታሌምን ሰዎች ወደ ቃዴስ ጠራቸው፤ ዐሥር ሺሕ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም ዐብራው ሄደች።
11በዚያ ጊዜ ቄናዊው ሔቤር፣ የሙሴ ዐማች የኦባብ ልጆች ከሆኑት ከሌሎቹ ቄናውያን ተለይቶ በቃዴስ አጠገብ ጻዕናይም ከተባለ ቦታ ከሚገኘው ትልቅ ወርካ ጥግ ድንኳኑን ተክሎ ነበር።
12የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱን ሲሣራ በሰማ ጊዜ፣ 13ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከአሪሶት ሐጎይም እስከ ቂሶን ወንዝ ያለውን ሰራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ።
14በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባርቅን፣ “ተነሣ! እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሰጠባት ቀን ይህች ናት፤ እነሆ እግዚአብሔር በፊትህ ቀድሞ ወጥቷል” አለችው። ስለዚህ ባራቅ ዐሥር ሺሕ ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ። 15እግዚአብሔር ሲሣራንና ሠረገሎቹን ሁሉ በባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት እጅግ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ።
16ባርቅ ግን የሲሣራን ሠረገሎችና ሰራዊቱን እስከ አሪሶት ሐጎይም ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራ ሰራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። 17በአሦር ንጉሥ በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ጐሣ መካከል መልካም ግንኙነት ስለ ነበር ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሮጠ።
18ኢያዔልም ወጥታ ሲሣራን ተቀበለችውና፣ “ጌታዬ፤ ወደ ውስጥ ግባ፤ ፈጽሞ አትፍራ” አለችው፤ ሲሣራም ወደ ድንኳኗ ገባ፤ እርሷም በልብስ ሸፍና ደበቀችው።
19ሲሣራም፣ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ዕቃውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደ ገናም ሸፈነችው።
20እርሱም፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፣ ‘እዚህ ሰው አለ?’ ቢልሽ፣ ‘የለም’ በይ” አላት።
21የሔቤር ሚስት ኢያዔል ግን ሲሣራ ደክሞ፣ ከባድ እንቅልፍም ወስዶት ሳለ፣ የድንኳን ካስማና መዶሻ ይዛ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ከዚያም ካስማውን በመዶሻ ጆሮ ግንዱ ላይ መትታ ከመሬት ጋራ ሰፋችው፤ እርሱም ሞተ።
22ባርቅ ሲሣራን በመከታተል ላይ ስለ ነበር ከዚያ ሲደርስ፣ ኢያዔል ከድንኳኗ ወጥታ “ና፤ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፤ ስለዚህ ከርሷ ጋራ ወደ ድንኳኗ ገባ፤ ሲሣራም በጆሮ ግንዱ ላይ ካስማ እንደ ተመታበት ሞቶ ተዘርሮ ነበረ።
23በዚያች ዕለት እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤላውያን ፊት እንዲሸነፍ አደረገው፤ 24ከነዓናዊውን ንጉሥ ኢያቢስን እስኪደመስሱ ድረስ የእስራኤላውያን ክንድ እየበረታ ሄደ።
Currently Selected:
መሳፍንት 4: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.