መሳፍንት 2
2
የእግዚአብሔር መልአክ በቦኪም
1የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ‘ከእናንተ ጋራ የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ 2እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋራ ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤’ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድን ነው? 3ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፣ አማልክታቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።”
4የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ በተናገረ ጊዜ፣ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 5ያን ስፍራ ቦኪም#2፥5 ቦኪም ማለት አልቃሽ ማለት ነው። ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ።
ያለ መታዘዝ ውጤት
6ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ። 7ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።
8የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። 9እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በተምናሔሬስ ቀበሩት።
10ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። 11ከዚያም እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። 12ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም። እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤ 13እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አምልከዋልና 14እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው። 15እስራኤላውያን ለውጊያ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረውና እንደ ማለው ይሸነፉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ ተጨነቁ።
16 እግዚአብሔርም ከእነዚህ ወራሪዎች የሚያድኗቸውን መሳፍንት#2፥16 በዚህም ከ17-19 ባለው ክፍል መሪ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። አስነሣ፤ 17እስራኤላውያን ግን ሌሎችን አማልክት ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንታቸውን አልሰሙም። አባቶቻቸው እግዚአብሔርን በመታዘዝ በሄዱበት መንገድ ሳይሆን፣ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሕግ በመከተል ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ። 18እግዚአብሔር መሳፍንትን ባሰነሣላቸው ቍጥር ከመስፍኑ ጋራ ስለሚሆን፣ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ይራራላቸው ነበር። 19መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር።
20ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፤ “ይህ ሕዝብ ለቀደሙ አባቶቹ የሰጠሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፈ፣ እኔንም ስላልሰማ፣ 21ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው በምድሪቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንዳቸውንም እንኳ በፊታቸው አሳድጄ አላስወጣም። 22ይህን የማደርገውም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣ እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን መንገድ የሚጠብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ እፈትናቸው ዘንድ እነርሱን መሣሪያ ለማድረግ ነው።” 23ስለዚህ እግዚአብሔር እነዚያን ሕዝቦች በዚያው እንዲኖሩ አደረገ፤ በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት ወዲያውኑ አሳድዶ አላስወጣቸውም።
Currently Selected:
መሳፍንት 2: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.