ኢሳይያስ 66:19-24

ኢሳይያስ 66:19-24 NASV

“በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶቤልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ። ለእግዚአብሔር ቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላል እግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቍርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል። እኔም ካህናትና ሌዋውያን ይሆኑ ዘንድ አንዳንዶቹን እመርጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤ “ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ የሚበሏቸው ትሎች አይሞቱም፤ የሚያቃጥላቸው እሳታቸው አይጠፋም፤ ለሰውም ዘር ሁሉ አስጸያፊ ይሆናሉ።”