ኢሳይያስ 48
48
እልኸኛዪቱ እስራኤል
1“የያዕቆብ ቤት ሆይ፤
እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ፣
ከይሁዳ ዘር የተገኛችሁ፣
እናንተ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፣
በእውነት ወይም በጽድቅ ሳይሆን፣
የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ ይህን ስሙ!
2እናንተ የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን ብላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ፣
በእስራኤል አምላክ የምትታመኑ፣
ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው የሚለውን አድምጡ፤
3የቀደሙትን ነገሮች ከብዙ ዘመን በፊት ተናግሬአለሁ፤
ከአፌ ወጥተዋል፤ እንዲታወቁም አድርጌአለሁ፤
እኔም ድንገት ሠራሁ፤ እነርሱም ተፈጸሙ።
4የቱን ያህል እልኸኛ እንደ ነበርህ ዐውቃለሁና፤
የዐንገትህ ጅማት ብረት፣
ግንባርህም ናስ ነበር።
5ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ገና ድሮ ነገርሁህ፤
ከመፈጸማቸው በፊት አስታወቅሁህ፤ ይህም፣
‘ጣዖቶቼ ይህን አደረጉ፤
ከዕንጨት የተቀረጸው ምስልና ከብረት የተሠራው አምላኬ ይህን ወስኗል’
እንዳትል ነው።
6እነዚህን ነገሮች ሰምተሃል፤ ሁሉንም ተመልከታቸው፤
ራስህ ትክክለኛነታቸውን አትመሰክርምን?
“ከአሁን ጀምሮ አዳዲስ ነገሮችን፣
የተሰወሩብህን ያላወቅሃቸውን ነገሮች እነግርሃለሁ።
7እነርሱም የተፈጠሩት አሁን እንጂ ጥንት አይደለም፤
ስለ እነርሱም ከዛሬ በፊት አልሰማህም።
ስለዚህ፣ ‘አዎን፤ ስለ እነርሱ ዐውቃለሁ’
ማለት አትችልም።
8አልሰማህም ወይም አላወቅህም፤
ጆሮህ ከጥንት የተከፈተ አልነበረም፤
አንተ አታላይ እንደ ነበርህ፣
ከልጅነትህ ጀምሮ ዐመፀኛ መባልህን ዐውቄአለሁና።
9ስለ ስሜ ስል ቍጣዬን አዘገያለሁ፤
ስለ ምስጋናዬም ስል ከአንተ እገታዋለሁ፤
ይኸውም እንዳልቈርጥህ ነው።
10እነሆ፤ እንደ ብር ባይሆንም አንጥሬሃለሁ፤
በመከራ እቶን ፈትኜሃለሁ።
11ስለ ራሴ፣ ስለ ራሴ ስል አደርጋለሁ፤
ራሴን ለውርደት እንዴት አሳልፌ እሰጣለሁ?
ክብሬን ለማንም አልሰጥም።
እስራኤል ነጻ ሆነች
12“ያዕቆብ ሆይ፤
የጠራሁህ እስራኤል ሆይ፤ ስማኝ፤
እኔ እኔው ነኝ፤
ፊተኛው እኔ ነኝ፤ ኋለኛውም እኔ ነኝ።
13ምድርን የመሠረተች የእኔው እጅ ናት፤
ሰማያትን የዘረጋችም ቀኝ እጄ ናት፤
በምጠራቸው ጊዜ፣
ሁሉም በአንድነት ይቆማሉ።
14“ሁላችሁም በአንድነት ተሰብሰቡ፤ አድምጡም፤
ከጣዖቶች አስቀድሞ እነዚህን የተናገረ ማን ነው?
የእግዚአብሔር ምርጥ ወዳጅ የሆነ፣
እርሱ በባቢሎን#48፥14 ወይም በዚህና በ20 ላይ ከለዳውያን ላይ ያቀደውን እንዲፈጽም ያደርገዋል፤
ክንዱም በባቢሎናውያን ላይ ይሆናል።
15እኔ፣ እኔው ራሴ ተናግሬአለሁ፤
በርግጥ እኔ ጠርቼዋለሁ፤
አመጣዋለሁ፤
ሥራውም ይከናወንለታል።
16“ወደ እኔ ቅረቡ፤ ይህን ስሙ፤
“ከመጀመሪያ ጀምሮ በስውር አልተናገርሁም፤
ሲፈጸምም እኔ እዚያው ነበርሁ።”
አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ
ልከውኛል።
17የተቤዠህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣
የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣
መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ።
18ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣
ሰላምህ እንደ ወንዝ፣
ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።
19ዘርህ እንደ አሸዋ፣
ልጆችህ ስፍር እንደሌለው ትቢያ በሆኑ ነበር፤
ስማቸው አይወገድም፤
ከፊቴም አይጠፋም።”
20ከባቢሎን ውጡ፣
ከባቢሎናውያንም ሽሹ!
ይህን በእልልታ አስታውቁ፤ ዐውጁት፤
እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ተናገሩ፤
“እግዚአብሔር ባሪያውን ያዕቆብን
ተቤዥቶታል” በሉ።
21በምድረ በዳ ሲመራቸው አልተጠሙም ነበር፤
ውሃ ከዐለት አፈለቀላቸው፤
ዐለቱን ሰነጠቀ፤
ውሃውም በኀይል ፈልቆ ወጣ።
22“ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ኢሳይያስ 48: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.