የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 46

46
የባቢሎን አማልክት
1ቤል ተዋረደ፤ ናባው እጅግ ዝቅ አለ፤
ጣዖቶቻቸው በአጋሰስ ተጭነዋል#46፥1 ወይም አውሬና አጋሰስ ብቻ ናቸው
ይዘዋቸው የሚዞሩት ምስሎች ሸክም ናቸው፤
ለደከሙ እንስሳት ከባድ ጭነት ናቸው።
2እነርሱም በአንድ ላይ ዝቅ ይላሉ፤ ያጐነብሳሉ፤
ጭነቱን ለማዳን አይችሉም፤
ራሳቸውም በምርኮ ይወሰዳሉ።
3“እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤
የእስራኤል ቤት ቅሬታ ሁሉ፣
ከተፀነሳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የያዝኋችሁ፣
ከተወለዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የተሸከምኋችሁ ስሙኝ።
4እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣
የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ።
ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤
እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ።
5“ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋራ እኩል ታደርጉኛላችሁ?
እንመሳሰልስ ዘንድ ከማን ጋራ ታነጻጽሩኛላችሁ?
6ሰዎች ወርቅ ከከረጢታቸው ይዘረግፋሉ፤
ብርንም በሚዛን ይመዝናሉ፤
አንጥረኛን ይቀጥራሉ፤ እርሱም አምላክ አድርጎ ያበጅላቸዋል።
እነርሱም ይሰግዱለታል፤ ያመልኩታልም።
7አንሥተው በትከሻቸው ይሸከሙታል፤
እቦታው ያደርጉታል፤ በዚያም ይቆማል፤
ከዚያም ቦታ አይንቀሳቀስም፤
ማንም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይመልስም፤
ከጭንቀቱም አያድነውም።
8“እናንተ በደለኞች፣ ይህን አስታውሱ፤
አስቡበትም፤ በልባችሁም ያዙት።
9የጥንቱን፣ የቀደመውን ነገር አስታውሱ፤
እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤
እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም።
10የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣
ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ፤
‘ምክሬ የጸና ነው፤
ደስ የሚያሠኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።
11ከምሥራቅ ነጣቂ አሞራ፣
ከሩቅ ምድር ዐላማዬን የሚፈጽም ሰው እጠራለሁ።
የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤
ያቀድሁትን እፈጽማለሁ።
12እናንተ ልበ ደንዳኖች፣
ከጽድቅም የራቃችሁ ስሙኝ።
13ጽድቄን እያመጣሁ ነው፤
ሩቅም አይደለም፤
ማዳኔም አይዘገይም።
ለጽዮን ድነትን፣
ለእስራኤል ክብሬን አጐናጽፋለሁ።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 46: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ