ኢሳይያስ 36
36
የሰናክሬም ዛቻ በኢየሩሳሌም ላይ
1ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው። 2የአሦር ንጉሥ የጦር አዛዡን ከብዙ ሰራዊት ጋራ ከለኪሶ፣ ንጉሡ ሕዝቅያስ ወዳለበት፣ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። የጦር አዛዡም ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ፣ በላይኛው ኵሬ ቦይ አጠገብ ደርሶ ቆመ፤ 3የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።
4የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤
“ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው? 5የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ባዶ ቃል ብቻ ትናገራለህ። በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተደግፈህ ነው? 6እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብጽ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት! የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው። 7ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን?
8“ ‘አሁን ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋራ ተደራደር፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ! 9የምትመካው በግብጽ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ? 10ደግሞስ ይህን ምድር ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት ያለ እግዚአብሔር ይመስልሃልን? በዚህች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ”
11ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት።
12ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ቃሎች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኵስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው።
13የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ! 14ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ‘ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ እርሱ ሊያድናችሁ አይችልምና!’ 15ደግሞም ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር ንጉሥ ዐልፋ አትሰጥም’ እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
16“ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋራ ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ 17ይኸውም፣ የእናንተኑ ወደምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል የእንጀራና የወይን ምድር ወደሆነችው፣ እስካገባችሁ ድረስ ነው።’
18“ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት አያሳስታችሁ፤ ለመሆኑ፣ ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ከአሕዛብ አማልክት የትኛው ነው? 19የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክትስ የት ደረሱ? እነዚህ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 20ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ፣ አገሩን ከእጄ የታደገ የትኛው ነው? ታዲያ፣ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዴት ከእጄ ሊታደጋት ይችላል?”
21ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና።
22ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ መዝጋቢው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የጦር አዛዡ የተናገረውንም ሁሉ ነገሩት።
Currently Selected:
ኢሳይያስ 36: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.