የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 32

32
የጽድቅ መንግሥት
1እነሆ፤ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፤
ገዦችም በፍትሕ ይገዛሉ።
2እያንዳንዱ ሰው ከነፋስ መከለያ፣
ከወጀብም መጠጊያ ይሆናል።
በበረሓም እንደ ውሃ ምንጭ፣
በተጠማም ምድር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።
3የሚያዩ ሰዎች ዐይን ከእንግዲህ አይጨፈንም፤
የሚሰሙም ጆሮዎች ነቅተው ያደምጣሉ።
4የችኵል አእምሮ ያውቃል፤ ያስተውላልም፤
የተብታባም ምላስ የተፈታ ይሆናል፤
አጥርቶም ይናገራል።
5ከእንግዲህ ሰነፍ ጨዋ አይባልም፤
ጋጠወጥም አይከበርም።
6ሰነፍ ስንፍናን ይናገራል፤
አእምሮው ክፋትን ያውጠነጥናል፤
ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌለበትን አድራጎት ይፈጽማል፤
እግዚአብሔርም ላይ የስሕተት ቃል ይናገራል፤
ለተራበ ምግብ ይከለክላል፤
ለተጠማ ውሃ አይሰጥም።
7የጋጠወጥ ዘዴ ክፉ ነው፤
የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆን፣
ድኻን በሐሰት ለማጥፋት፣
ክፋት ያውጠነጥናል።
8ጨዋ ግን ሐሳቡም ጨዋ ነው፤
በጨዋነት ምግባርም ጸንቶ ይገኛል።
የኢየሩሳሌም ሴቶች
9እናንተ ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች፣
ተነሡ፤ ድምፄን ስሙ፤
እናንተ ተደላድላችሁ የምትኖሩ ሴቶች ልጆች ሆይ፤
የምነግራችሁን አድምጡ!
10ዓመቱ ገና እንዳለፈ፣
ተደላድላችሁ የነበራችሁ ትንቀጠቀጣላችሁ፤
የወይን ተክል ፍሬ አይሰጥም፤
የፍራፍሬም ወቅት አይመጣም።
11እናንተ ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች ተንቀጥቀጡ፤
እናንተ ተደላድላችሁ የምትኖሩ ሴቶች ልጆች፣ በፍርሀት ተርበትበቱ!
ልብሳችሁን አውልቁ፤
ወገባችሁን በማቅ ታጠቁ።
12ስለ ለሙ መሬት ደረታችሁን ምቱ፤
ስለ ፍሬያማው የወይን ተክል ዕዘኑ፤
13ስለ ሕዝቤ ምድር፣
እሾኽና አሜከላ ስለ በቀለበት ምድር፣
ስለ ፈንጠዝያ ቤቶች ሁሉ፣
ስለዚህችም መፈንጫ ከተማ አልቅሱ።
14ዐምባ ምሽጉ ወና ይሆናል፤
ውካታ የበዛበት ከተማ ጭር ይላል፤
ምሽጉና ማማው ለዘላለሙ ዋሻ፣
የዱር አህያ መፈንጫ፣ የመንጋም መሰማሪያ ይሆናል፤
15ይህም የሚሆነው መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፣
ምድረ በዳው ለም መሬት፣
ለሙ መሬትም ጫካ እስኪመስል ድረስ ነው።
16በምድረ በዳ ፍትሕ ይሰፍናል፤
በለሙም መሬት ጽድቅ ይኖራል፤
17የጽድቅ ፍሬ ሰላም፣
የጽድቅ ውጤትም ጸጥታና ለዘላለም ያለ ሥጋት ይሆናል።
18ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣
በሚያስተማምን ቤት፣
ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።
19ደኑ በበረዶ ቢመታ፣
ከተማውም ፈጽሞ ቢወድም፣
20በየወንዙ ዳር ዘር የምትዘሩ፣
በሬዎቻችሁንና አህዮቻችሁን በነጻነት የምታሰማሩ፣
ምንኛ ብፁዓን ናቸው።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 32: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ