ሆሴዕ 6
6
የእስራኤል ንስሓ አለመግባት
1“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤
እርሱ ሰባብሮናል፤
እርሱም ይጠግነናል፤
እርሱ አቍስሎናል፤
እርሱም ይፈውሰናል።
2ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤
በርሱም ፊት እንድንኖር፣
በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል።
3 እግዚአብሔርን እንወቀው፤
የበለጠ እናውቀውም ዘንድ አጥብቀን እንከተለው፤
እንደ ንጋት ብርሃን፣
በርግጥ ይገለጣል፤
ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣
እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።”
4“ኤፍሬም ሆይ፤ ምን ላድርግህ?
ይሁዳ ሆይ፤ ምን ላድርግህ?
ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ጉም፣
እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ ነው።
5ስለዚህ በነቢያቴ ቈራረጥኋችሁ፤
በአፌም ቃል ገደልኋችሁ፣
ፍርዴም እንደ መብረቅ በላያችሁ አበራ።
6ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣
ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ አምላክን ማወቅ እወድዳለሁ።
7እንደ አዳም#6፥7 ወይም በአዳም እንደ ሆነው ወይም በሰዎች ቃል ኪዳንን ተላለፉ፤
በዚያም ለእኔ ታማኝ አልነበሩም።
8ገለዓድ በደም የተበከለች፣
የክፉዎች ሰዎች ከተማ ናት።
9ወንበዴዎች ሰውን ለማጥቃት እንደሚያደቡ፣
ካህናትም በቡድን እንዲሁ ያደርጋሉ፤
በሴኬም መንገድ ላይ ሰዎችን ይገድላሉ፤
አሳፋሪም ወንጀል ይፈጽማሉ።
10በእስራኤል ቤት የሚሰቀጥጥ ነገር አይቻለሁ፤
በዚያ ኤፍሬም ዘማዊ ሆነ፤
እስራኤልም ረከሰ።
11“ይሁዳ ሆይ፤ ለአንተም፣
መከር ተመድቦብሃል።
“ሕዝቤን ከምርኮ አገር በመለስሁ ጊዜ፣
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.