የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዕብራውያን 4:1-12

ዕብራውያን 4:1-12 NASV

እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት የተሰጠው ተስፋ አሁንም የተጠበቀ ስለሆነ፣ ከእናንተ ማንም ለዚያ ሳይበቃ እንዳይቀር እንጠንቀቅ፤ ለእነዚያ እንደ ተሰበከ ለእኛም ደግሞ የምሥራቹ ቃል ተሰብኮልናልና። ነገር ግን ሰሚዎቹ ቃሉን ከእምነት ጋር ስላላዋሐዱት አልጠቀማቸውም። እኛ ያመንነው ግን ወደዚያ ዕረፍት እንገባለን፤ እግዚአብሔርም፣ “ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤ ‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም’ ” ብሏል። ይሁን እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የእርሱ ሥራ ተከናውኗል። ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሏልና። ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣ “ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም” ይላል። ወደ ዕረፍቱ ገና የሚገቡ አንዳንዶች አሉ፤ ቀድሞ የምሥራቹ ቃል የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ዕረፍት አልገቡም። ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ዛሬ” ብሎ እንደ ገና አንድን ቀን ወሰነ፤ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት በኩል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ ልባችሁን አታደንድኑ” ተብሎ ቀደም ሲል እንደ ተነገረው ነው። ኢያሱ ዕረፍትን ሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። ስለዚህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገና ቀርቶለታል፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚገባ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱም ደግሞ ከሥራው ያርፋል። እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ፣ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።