እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን፤ በእጃችሁ ተሰጥተዋል። ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ። “ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ። ሰውን የገደለ ሁሉ ስለ ሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ። “የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ፣ ደሙ በሰው እጅ ይፈስሳል፤ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አምሳል፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን ሠርቶታልና። እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሰራፋ።” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና አብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንስሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ። ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣ ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን ዐስባለሁ።” ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው።
ዘፍጥረት 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 9
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 9:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos