የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 35:1-29

ዘፍጥረት 35:1-29 NASV

እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያዕቆብን፣ “ተነሥና ወደ ቤቴል ውጣ፤ እዚያም ተቀመጥ፤ ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድህ ጊዜ ለተገለጠልህ አምላክ (ኤል) በዚያ መሠዊያ ሥራ” አለው። ስለዚህም ያዕቆብ ለቤቱ ሰዎችና አብረውት ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ። ተነሥተን ወደ ቤቴል እንውጣ፤ እዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፣ በሄድሁበትም ስፍራ ሁሉ ላልተለየኝ አምላክ (ኤል) መሠዊያ እሠራለሁ።” ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሰብስበው፣ የጆሮ ጕትቾቻቸውን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት። ያዕቆብም ወስዶ ሴኬም አጠገብ ካለው ወርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው። ያንንም ቦታ ለቅቀው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በዙሪያቸው በነበሩት ከተሞች ሁሉ ላይ ፍርሀትና ድንጋጤ ስለ ለቀቀባቸው ያሳደዳቸው አልነበረም። ያዕቆብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ፣ በከነዓን ወደምትገኘው፣ ቤቴል ወደተባለችው ወደ ሎዛ ደረሱ። ያዕቆብም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ ስሙን ኤል-ቤቴል አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የተገለጠለት በዚህ ቦታ ነበር። በዚህ ጊዜ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፤ ከቤቴል ዝቅ ብሎ በሚገኘው ወርካ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ከዚህ የተነሣም ያ ቦታ አሎንባኩት ተባለ። ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለያዕቆብ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ ባረከውም። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ ነበረ፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው። ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ነኝ፤ ብዛ ተባዛ፤ ሕዝብና የሕዝቦች ማኅበር ከአንተ ይወጣሉ፤ ነገሥታትም ከአብራክህ ይከፈላሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችኑ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። ያዕቆብ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፤ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቍርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት። ያዕቆብም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው። ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፤ ምጡም ጠናባት። ምጡ አስጨንቋት ሳለ፣ አዋላጇ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገይ ነው” አለቻት። እርሷ ግን ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች፣ ልጇን ቤንኦኒ አለችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተ ልሔም ተቀበረች። ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከ ዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው። እስራኤልም ጕዞውን በመቀጠል ከጋዴር ወንዝ ባሻገር ድንኳኑን ተከለ። እስራኤልም በዚያ ምድር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር ተኛ፤ እስራኤልም ድርጊቱን ሰማ። ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም፦ የልያ ልጆች፦ የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤ የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍ፣ ብንያም፤ የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ ዳን፣ ንፍታሌም፤ የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ ጋድ፣ አሴር ናቸው። እነዚህ ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ወንዶች ልጆች ነበሩ። ያዕቆብ አባቱ ወዳለበት ወደ መምሬ መጣ፤ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩባት፣ ቂርያትአርባቅ ወይም ኬብሮን የተባለችው ቦታ ናት። ይስሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤ አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}