የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 3:1-15

ዘፍጥረት 3:1-15 NASV

እባብ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሏልን?” አላት። ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።” እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከርሷም ጋራ ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ። ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሚስቱ ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው። አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋራ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች። እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣ “ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}