ዘፍጥረት 25:1-34

ዘፍጥረት 25:1-34 NASV

አብርሃም ኬጡራ የተባለች ሌላ ሚስት አገባ። እርሷም፦ ዘምራንን፣ ዮቅሳንን፣ ሜዳንን፣ ምድያምን፣ የስቦቅንና ስዌሕን ወለደችለት። ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ፤ የድዳንም ልጆች፦ አሦራውያን፣ ለጡሳውያንና ለኡማውያን ናቸው። የምድያም ልጆች፦ ጌፌር፣ ዔፌር፣ ሄኖኅ፣ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይሥሐቅ አወረሰው፤ ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይሥሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው። አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ ዐምስት ዓመት ኖረ። ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ልጆቹ ይሥሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ። አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ይሥሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይሥሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር። ግብጻዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው። የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦ የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣ ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣ ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣ ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣ ናፌስና ቄድማ። እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው። እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብጽ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋራ በጠላትነት ኖሩ። የአብርሃም ልጅ የይሥሐቅ ትውልድ ይህ ነው። አብርሃም ይሥሐቅን ወለደ፤ ይሥሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች። ይሥሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች። ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሄደች። እግዚአብሔርም እንዲህ አላት፤ “ሁለት ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” አላት። የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀኗ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጕር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ። ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይሥሐቅ የስድሳ ዓመት ሰው ነበር። ልጆቹም ዐደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። ይሥሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወድደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድደው ነበር። አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም፣ “እነሆ፤ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ። ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት። ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}