የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 21

21
የይሥሐቅ መወለድ
1 እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት ሣራን ዐሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት። 2ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። 3አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይሥሐቅ#21፥3 ይሥሐቅ ማለት ይሥቃል ማለት ነው። አለው። 4አብርሃም፣ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ልጁን ይሥሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው። 5አብርሃም፣ ልጁ ይሥሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ።
6ሣራም፣ “እግዚአብሔር ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋራ ይሥቃል” አለች። 7ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች።
የአጋርና የእስማኤል መባረር
8ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይሥሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። 9በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብጻዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይሥሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ 10አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርራት፤ የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይሥሐቅ ጋራ አይወርስምና” አለችው።
11እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። 12እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይሥሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። 13የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።”
14በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር።
15በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። 16ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም#21፥16 ዕብራይስጡና ሰብዓ ሊቃናት ልጁ ይላሉ። እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር።
17እግዚአብሔርም የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። 18ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።”
19እግዚአብሔርም ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።
20እግዚአብሔር ከልጁ ጋራ ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ። 21በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብጽ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው።
በቤርሳቤህ የተደረገው ስምምነት
22በዚያ ጊዜ አቢሜሌክ ከሰራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋራ ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው። 23እንግዲህ እኔንና ልጆቼን፣ ዘሬንም በመሸንገል አንዳች ክፉ ነገር እንዳታደርስብን በእግዚአብሔር ፊት ማልልኝ። እኔ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ፣ አንተም ለእኔና በእንግድነት ለተቀመጥህባት ለዚህች ምድር ቸርነት አድርግ።”
24አብርሃምም፣ “ዕሺ፤ እምላለሁ” አለ።
25ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮች ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጕድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት። 26አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው።
27ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ። 28አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤ 29አቢሜሌክም፣ “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለይተህ ለብቻ ያቆምሃቸው ለምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው።
30አብርሃምም፣ “ይህን የውሃ ጕድጓድ የቈፈርሁ እኔ ለመሆኔ ምስክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ዕንካ ተቀበለኝ” አለው።
31ስለዚህ ቦታው፣ ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ ቤርሳቤህ#21፥31 ቤርሳቤህ ማለት ሰባት የውሃ ጕድጓድ ወይም የመሐላ የውሃ ጕድጓድ ማለት ሊሆን ይችላል። ተባለ።
32በቤርሳቤህ የስምምነት ውል ካደረጉ በኋላ፣ አቢሜሌክና የሰራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ተመለሱ። 33አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም እግዚአብሔር የዘላለም አምላክን ስም ጠራ። 34አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረዥም ጊዜ በእንግድነት ኖረ።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 21: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ