የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ገላትያ 4:21-31

ገላትያ 4:21-31 NASV

እናንተ ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስኪ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን? አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፏልና። ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነበር። እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት። እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋራ በባርነት ናትና። ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት። እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣ በእልልታ ጩኺ፤ ባል ካላት ይልቅ፣ የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።” እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይሥሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። በዚያ ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው ልጅ፣ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከነልጇ አባርራት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋራ አይወርስምና።” ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።