የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም በእግዚአብሔር መንፈስ አወጣኝ፤ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ ሸለቆውም በዐጥንቶች ተሞልቶ ነበር። በእነርሱም መካከል ወደ ፊትና ወደ ኋላ አመላለሰኝ፤ በሸለቆውም ወለል ላይ በጣም የደረቁ እጅግ ብዙ ዐጥንቶች አየሁ። እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ብቻ ታውቃለህ” አልሁ። ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንት ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ! ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ። ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቈዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ” ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ። እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቈዳም ሸፍኗቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም። ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’ ” ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ዐጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ የለንም፤ ተቈርጠናል።’ ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።
ሕዝቅኤል 37 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 37
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 37:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos