ዘፀአት 9:27-35

ዘፀአት 9:27-35 NASV

ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አሁንስ በድያለሁ፤ እግዚአብሔር ትክክል ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ስተናል። መብረቅና በረዶ በዝቶብናልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ በዚህ የመኖር ግዴታ የለባችሁም።” ሙሴም መልሶ፣ “ከከተማዋ በወጣሁ ጊዜ፣ እጆቼን ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ አንተም ምድር የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቅ ዘንድ መብረቁ ያቆማል፤ ከእንግዲህ በኋላ በረዶ አይኖርም። ሆኖም አንተና ሹማምትህ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር አምላክን እንደማትፈሩ ዐውቃለሁ።” ተልባው አብቦ፣ ገብሱም ፍሬ ይዞ ስለ ነበር፣ ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። ስንዴውና አጃው ግን በዚያ ወቅት ባለማፍራቱ አልጠፋም ነበር። ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማው ወጣ። እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ቆመ፤ ዝናቡም በምድሪቱ ላይ መዝነቡን አቆመ። ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጐድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደ ገና በደለ፤ እርሱና ሹማምቱ ልባቸውን አደነደኑ። ስለዚህ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም እስራኤላውያን ይሄዱ ዘንድ አልለቀቃቸውም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}