ዘፀአት 40
40
የማደሪያውን ድንኳን መትከል
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2“ማደሪያውን ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን በወሩ የመጀመሪያ ቀን ትከለው፤ 3የምስክሩን ታቦት በውስጡ አኑር፤ ታቦቱንም በመጋረጃው ጋርደው። 4ጠረጴዛውንም ወደ ውስጥ አምጥተህ ዕቃዎቹን በላዩ ላይ አሰናዳ፤ ከዚያም መቅረዙን አስገብተህ መብራቶቹን በቦታቸው አስቀምጥ። 5የዕጣኑን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ለፊት አስቀምጠው፤ ከማደሪያውም መግቢያ ላይ መጋረጃውን አድርግ።
6“የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በማደሪያው መግቢያ ፊት ለፊት፣ በመገናኛው ድንኳን አስቀምጠው። 7የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑርበት፤ ውሃም አኑርበት። 8በዙሪያውም የአደባባዩን ቅጥር ትከል፤ መጋረጃውንም በአደባባዩ መግቢያ ላይ አድርገው።
9“ቅብዐ ዘይቱን ወስደህ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቅባ፤ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ቀድስ፤ የተቀደሰም ይሆናል። 10ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቅባ፤ መሠዊያውን ቀድስ፣ እጅግም የተቀደሰ ይሆናል። 11የመታጠቢያው ሰንና ማስቀመጫውን ቅባ፤ ቀድሳቸውም።
12“አሮንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ አምጥተህ በውሃ ዕጠባቸው። 13ከዚያም አሮንን የተቀደሰውን ልብስ አልብሰው፤ ካህን ሆኖ ያገለግለኝ ዘንድ ቅባው፤ ቀድሰውም። 14ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ሸሚዝ አልብሳቸው። 15ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን እንደ ቀባህ ቅባቸው፤ መቀባታቸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለሚቀጥል ክህነት ነው።” 16ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።
17እንዲሁም በሁለተኛው ዓመት፣ የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የማደሪያው ድንኳን ተተከለ። 18ሙሴ የማደሪያውን ድንኳን በተከለ ጊዜ፣ መቆሚያዎቹን በቦታቸው አኖረ፤ ወጋግራዎቹን አቆመ፤ አግዳሚዎቹን አስገባ፤ ምሰሶዎቹንም ተከለ። 19ከዚያም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ፣ መደረቢያውንም በድንኳኑ ላይ ዘረጋው።
20ምስክሩን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አስቀመጠው፤ መሎጊያዎቹንም ከታቦቱ ጋራ አያያዛቸው፤ የስርየት መክደኛውንም በላዩ ላይ አደረገው። 21ከዚያም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ታቦቱን ወደ ማደሪያው ድንኳን አስገብቶ መከለያ መጋረጃውን ሰቀለ፤ የምስክሩንም ታቦት ጋረደው።
22ሙሴ ጠረጴዛውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፣ ከማደሪያው በስተሰሜን ከመጋረጃው ውጭ አኖረው፤ 23እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ኅብስቱን በላዩ ላይ በእግዚአብሔር ፊት አኖረ።
24መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከጠረጴዛው ትይዩ ከማደሪያው ድንኳን በስተ ደቡብ በኩል አኖረው፤ 25እግዚአብሔር እንዳዘዘውም መብራቶቹን በእግዚአብሔር ፊት አበራ።
26ሙሴ የወርቅ መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው ፊት ለፊት አኖረው፤ 27እግዚአብሔር እንዳዘዘውም መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣን አጠነበት።
28ከዚያም መጋረጃውን በማደሪያው ድንኳን መግቢያ ላይ ሰቀለው። 29የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንም በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ አኖረው፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን መሥዋዕት በላዩ ላይ አቀረበ።
30የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀመጠ፤ ለመታጠቢያም ውሃ አደረገበት፤ 31ሙሴና አሮን፣ ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበት ነበር። 32እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡና ወደ መሠዊያው በቀረቡ ቍጥር ይታጠቡ ነበር።
33ከዚያም ሙሴ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ በአደባባዩም መግቢያ ላይ መጋረጃውን ሰቀለ፤ እንደዚህ አድርጎ ሙሴ ሥራውን ፈጸመ።
የእግዚአብሔር ክብር
34ከዚያም ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ። 35ደመናው በላዩ ላይ ስለ ነበረና የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላው፣ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም።
36በእስራኤላውያን ጕዞ ሁሉ ደመናው ከማደሪያው ላይ በተነሣ ጊዜ፣ ይጓዙ ነበር፤ 37ደመናው ካልተነሣ ግን፣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38ስለዚህ በጕዟቸው ሁሉ ወቅት፣ በእስራኤል ቤት ፊት ሁሉ የእግዚአብሔር ደመና በቀን ከማደሪያው በላይ፣ በሌሊትም እሳቱ በደመናው ውስጥ ነበር።
Currently Selected:
ዘፀአት 40: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.