መክብብ 5
5
እግዚአብሔርን ፍራ
1ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማት መቅረብ የሞኞችን መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ እነርሱ ክፉ እንደሚሠሩ አያውቁምና።
2በአፍህ አትፍጠን፤
በአምላክም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣
በልብህ አትቸኵል፤
አምላክ በሰማይ፣
አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤
ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን።
3በሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ፣
ብዙ ቃል ባለበትም የሞኝ ንግግር ይገለጣል።
4ለአምላክ ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሞኞች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም። 5ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል። 6አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። አምላክ በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ? 7ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ አምላክን ፍራ።
ባለጠግነት ከንቱ ነው
8በአገር ውስጥ ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ በእነዚህ በሁለቱም ላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ። 9ከምድሩ የሚገኘው ትርፍ ለሁሉም ነው፤ ንጉሡም ራሱ የሚጠቀመው ከዕርሻ ነው።
10ገንዘብን የሚወድድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤
ብልጽግናም የሚወድድ፣ በትርፉ አይረካም፤
ይህም ከንቱ ነው።
11ሀብት በበዛ ቍጥር፣
ተጠቃሚውም ይበዛል፤
በዐይኑ ብቻ ከማየት በቀር
ታዲያ፣ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?
12ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣
የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤
የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን
እንቅልፍ ይነሣዋል።
13ከፀሓይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፦
ይህም ለባለቤቱ ጕዳት የተከማቸ ሀብት፣
14ወይም በአንድ መጥፎ አጋጣሚ የጠፋ ብልጽግና ነው፤
ልጅ ሲወልድም፣
ለርሱ የሚያስቀርለት ምንም ነገር አይኖርም።
15ሰው ከእናቱ ማሕፀን ዕራቍቱን ይወለዳል፤
እንደ መጣው እንዲሁ ይመለሳል።
ከለፋበትም ነገር፣
አንድም እንኳ በእጁ ይዞ ሊሄድ አይችልም።
16ይህ ደግሞ እጅግ ክፉ ነገር ነው፤
ሰው እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤
የሚደክመው ለነፋስ ስለ ሆነ፣
ትርፉ ምንድን ነው?
17በብዙ ጭንቀት፣ መከራና ብስጭት፣
ዘመኑን ሁሉ በጨለማ ውስጥ ይበላል።
18የሰው ዕጣው ይህ ስለ ሆነ፣ አምላክ በሰጠው በጥቂት ዘመኑ ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ነገር ርካታን ያገኝ ዘንድ፣ መብላቱና መጠጣቱም መልካምና ተገቢ መሆኑን ተገነዘብሁ። 19አምላክ ለሰው ባለጠግነትና ሀብት መስጠቱ፣ እንዲደሰትበትም ማስቻሉ፣ ዕጣውን እንዲቀበልና በሥራውም እንዲደሰት ማድረጉ፣ ይህ የአምላክ ስጦታ ነው። 20አምላክ የልብ ደስታ ስለሚሰጠውም በሕይወቱ ዘመን ያሉትን ቀናት እምብዛም አያስባቸውም።
Currently Selected:
መክብብ 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.