ዘዳግም 23
23
ከእግዚአብሔር ጉባኤ መለየት
1ብልቱ የተቀጠቀጠ ወይም የተቈረጠ ማንኛውም ሰው ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።
2ዲቃላም ይሁን የዲቃላው ዘር የሆነ ሁሉ፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።
3አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማንኛውም የርሱ ዘር፣ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ቢሆን ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። 4ምክንያቱም ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በጕዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር#23፥4 ይኸውም ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ነው። ይኖር የነበረውን የቢዖር ልጅ በለዓምን አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዙት። 5ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን አልሰማውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ስለሚወድድህ ርግማኑን በረከት አደረገልህ። 6በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ሰላምን ለእነርሱ አትመኝ።
7ወንድምህ ስለ ሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብጻዊውን አትጥላው። 8ለእነርሱ የተወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ መግባት ይችላሉ።
የጦር ሰፈር ንጽሕና አጠባበቅ
9ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በሰፈርህ ጊዜ፣ ከማናቸውም ርኩሰት ራስህን ጠብቅ። 10ከመካከላችሁ ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር፣ ከሰፈር ወጥቶ እዚያው ይቈይ። 11እየመሸ ሲመጣ ግን ገላውን ይታጠብ፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ወደ ሰፈሩ ይመለስ።
12ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ። 13ከትጥቅህም ጋራ መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት። 14አምላክህ እግዚአብሔር ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን።
ልዩ ልዩ ሕጎች
15አንድ ባሪያ ከአሳዳሪው ኰብልሎ ወደ አንተ ቢመጣ፣ ለአሳዳሪው አሳልፈህ አትስጠው። 16ደስ በሚያሠኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው።
17ወንድ ወይም ሴት እስራኤላዊ የቤተ ጣዖት አመንዝራ አይሁን። 18ለዝሙት ዐዳሪ ሴት ወይም ለወንደቃ#23፥18 ዕብራይስጡ፣ ውሻ ይላል። የተከፈለውን ዋጋ ለማንኛውም ስእለት አድርገህ ለመስጠት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታምጣ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ሁለቱንም ይጸየፋቸዋልና።
19የገንዘብ፣ የእህል ወይም የማንኛውንም ነገር ወለድ ለማግኘት ለወንድምህ በወለድ አታበድር። 20ባዕድ ለሆነ ሰው ወለድ ማበደር ትችላለህ፤ ነገር ግን ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እጅህ በሚነካው በማናቸውም ነገር አምላክህ እግዚአብሔር እንዲባርክህ ለእስራኤላዊ ወንድምህ በወለድ አታበድረው።
21ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት ከተሳልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር አጥብቆ ከአንተ ይሻዋልና፣ ኀጢአት እንዳይሆንብህ ለመክፈል አትዘግይ። 22ሳትሳል ብትቀር ግን በደለኛ አትሆንም። 23በአንደበትህ የተናገርኸውን ሁሉ ለመፈጸም ጠንቃቃ ሁን፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በገዛ አንደበትህ ፈቅደህ ስእለት ተስለሃልና።
24ወደ ባልንጀራህ የወይን ተክል ቦታ በምትገባበት ጊዜ፣ ያሠኘህን ያህል መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን አንዳችም በዕቃህ አትያዝ። 25ወደ ባልንጀራህ ዕርሻ በምትገባበት ጊዜ፣ እሸት መቅጠፍ ትችላለህ፤ በሰብሉ ላይ ግን ማጭድ አታሳርፍበት።
Currently Selected:
ዘዳግም 23: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.