የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 20

20
ለጦርነት መውጣት
1ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና። 2ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፣ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሰራዊቱ ይናገር፤ 3እንዲህም ይበል፤ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤ 4ድልን ያቀዳጃችሁ ዘንድ ስለ እናንተ ጠላቶቻችሁን ሊወጋ ዐብሯችሁ የሚወጣው አምላካችሁ እግዚአብሔር ነውና።”
5አለቆቹም ለሰራዊቱ እንዲህ ይበሉ፤ “አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለን? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ቤቱን የሚያስመርቀው ሌላ ሰው ይሆናል። 6ወይን ተክሎ ገና ያልበላለት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ወይኑን ሌላ ሰው ይበላዋል። 7ሚስት አጭቶ ያላገባት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ አለዚያ በጦርነቱ ይሞትና ሌላ ሰው ያገባታል።” 8ከዚያም አለቆቹ፣ “የሚፈራ ወይም ልቡ የሚባባ ሰው አለን? የወንድሞቹም ልብ እንዳይባባ ወደ ቤቱ ይመለስ” በማለት ጨምረው ይናገሩ። 9አለቆቹ ለሰራዊቱ ተናግረው ሲያበቁ፣ አዛዦችን በሰራዊቱ ላይ ይሹሙ።
10አንድን ከተማ ለመውጋት በምትዘምትበት ጊዜ፣ አስቀድመህ ለሕዝቧ የሰላም ጥሪ አስተላልፍ፤ 11ከተቀበሉህና ደጃቸውን ከከፈቱልህ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ሕዝብ ሁሉ ገባርህ ይሁን፤ ያገልግልህም። 12ዕርቀ ሰላምን ባለመቀበል ውጊያን ከመረጡ፣ ከተማዪቱን ክበባት። 13አምላክህ እግዚአብሔር አሳልፎ በእጅህ በሰጠህ ጊዜ፣ በውስጧ ያሉትን ወንዶች በሙሉ በሰይፍ ግደላቸው። 14ነገር ግን ሴቶቹን ሕፃናትን፣ እንስሳቱንና በከተማዪቱ ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ነገር በምርኮ ለራስህ አድርግ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከጠላቶችህ የሚሰጥህን ምርኮ ልትጠቀምበት ትችላለህ። 15እንግዲህ የአካባቢህ አሕዛብ ከተሞች ባልሆኑትና ከአንተ እጅግ ርቀው በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ላይ የምታደርገው ይኸው ነው።
16አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በአሕዛብ ከተሞች ውስጥ፣ እስትንፋስ ያለውን ነገር አታስተርፍ። 17ኬጢያዊውን፣ አሞራዊውን፣ ከነዓናዊውን፣ ፌርዛዊውን፣ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት ፈጽመህ ደምስሳቸው#20፥17 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።18አለዚያ አማልክታቸውን በሚያመልኩበት ጊዜ የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሁሉ ታደርግ ዘንድ ያስተምሩሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔርም ላይ ኀጢአት ትሠራለህ።
19አንድን ከተማ ተዋግተህ ለመያዝ የረጅም ጊዜ ከበባ ካደረግህ፣ ዛፎቹን በመጥረቢያ ጨፍጭፈህ አታጥፋ፤ የእነርሱን ፍሬ መብላት ትችላለህና አትቍረጣቸው፤ ከብበህ የምታጠፋቸው የሜዳ ዛፎች ሰዎች ናቸውን?#20፥19 ወይም፣ ለመክበብ ወረደ፤ የዛፎቹ ፍሬ ለሰው ጥቅም ይዋሉ 20የሚበላ ፍሬ እንደማያፈራ የምታውቀውን ዛፍ ግን ልትቈርጠውና ጦርነት የምታካሂድባትን ከተማ በድል እስክትቈጣጠራት ድረስ ለከበባው ምሽግ መሥሪያ ልትጠቀምበት ትችላለህ።

Currently Selected:

ዘዳግም 20: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ