ዘዳግም 19
19
መማጸኛ ከተሞች
19፥1-14 ተጓ ምብ – ዘኍ 35፥6-34፤ ዘዳ 4፥41-43፤ ኢያ 20፥1-9
1አምላክህ እግዚአብሔር ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፣ 2አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፣ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ለይ። 3ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፣ በሦስት ክፈላቸው።
4በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው። 5እነሆ፤ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋራ ዕንጨት ለመቍረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፣ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል። 6አለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፣ መንገዱ ረዥም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል። 7ሦስት ከተሞችን ለራስህ እንድትለይ ያዘዝሁህ በዚሁ ምክንያት ነው።
8ለአባቶችህ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት፣ አምላክህ እግዚአብሔር ወሰንህን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቱን ሁሉ ሲሰጥህ፣ 9አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድድና ምን ጊዜም በመንገዱ እንድትሄድ ዛሬ የማዝዝህን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቅ ከሆነ፣ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ። 10አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስስና በሚፈስሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆን ይህን አድርግ።
11ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣ አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፣ ቢገድለውና ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፣ 12የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፤ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት። 13አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግድ።
14አምላክህ እግዚአብሔር እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ለአንተ በሚተላለፍልህ ርስት ላይ የቀድሞ ሰዎች ያስቀመጡትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አታንሣ።
ምስክሮች
15በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍ ሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ፣ አንድ ምስክር አይበቃም፤ ነገር በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች የምስክር አፍ መረጋገጥ አለበት።
16ተንኰለኛ የሆነ ምስክር አንድን ሰው በሐሰት ቢከስስ፣ 17ክርክሩ የሚመለከታቸው ሁለቱ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት፣ በዚያ ወቅት በሚያገለግሉት ካህናትና ፈራጆች ፊት ይቁሙ። 18ፈራጆችም ጕዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፤ ያም ምስክር በወንድሙ ላይ በሐሰት የመሰከረ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ 19በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በርሱ ላይ አድርጉበት፤ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ። 20የቀሩትም ሰዎች ይህን ሰምተው ይፈራሉ፤ እንዲህ ያለው ክፉ ነገርም ለወደፊቱ በመካከልህ ከቶ አይደገምም። 21ርኅራኄ አታድርግ፤ ሕይወት በሕይወት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር ይመለስ።
Currently Selected:
ዘዳግም 19: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.