የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 10

10
በድጋሚ የተሰጡ የመጀመሪያዎቹ ዐይነት ጽላት
1በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀርጸህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ላይ ውጣ፤ ታቦትም ከዕንጨት ሥራ። 2እኔም አንተ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላት ላይ የነበሩትን ቃላት በእነዚህኞቹ ጽላት ላይ እጽፋቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።”
3ስለዚህ ከግራር ዕንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀረጽሁ፤ ሁለቱንም ጽላት በእጆቼ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። 4እግዚአብሔር በስብሰባው ቀን፣ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የተናገራቸውንና ቀድሞ ጽፏቸው የነበሩትን ዐሥሩን ትእዛዞች በእነዚህ ጽላት ላይ ጻፋቸው። እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ። 5ከዚያም ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ፤ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት በሠራሁት ታቦትም ውስጥ፣ ጽላቱን አስቀመጥኋቸው፤ አሁንም እዚያ ናቸው።
6እስራኤላውያን ከብኤሮት ብኔያዕቃን፣ (ከያዕቃን ልጆች የውሃ ጕድጓዶች) ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤ ልጁ አልዓዛር በርሱ ምትክ ካህን ሆነ። 7ከዚያም ተነሥተው ጉድጎዳ ወደ ተባለ ስፍራ፣ ቀጥሎም የውሃ ፈሳሾች ወዳሉባት ዮጥባታ ወደምትባል ምድር ተጓዙ። 8በዚያ ጊዜ፣ ዛሬም እንደሚያደርገው ያገለግል ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም ፊት እንዲቆምና በስሙ እንዲባርክ የእግዚአብሔርንም የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም እግዚአብሔር የሌዊን ነገድ ለየ። 9ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር ነው።
10እኔም በመጀመሪያው ጊዜ እንዳደረግሁት፣ በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ በዚህ ጊዜም እግዚአብሔር እንደ ገና ሰማኝ፤ እግዚአብሔር አንተን ሊያጠፋ አልፈቀደም። 11ስለዚህም እግዚአብሔር፣ “ሂድ፤ ለአባቶቻቸው ለመስጠት ወደ ማልሁላቸው ምድር ገብተው እንዲወርሱ ሕዝቡን ምራ” አለኝ።
እግዚአብሔርን ፍራ
12አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣ 13መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና የእግዚአብሔር ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?
14ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው። 15ነገር ግን እግዚአብሔር አባቶችህን ስላፈቀረ፣ ወደዳቸው፤ ዛሬም እንደ ሆነው የእነርሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከአሕዛብ ሁሉ ለይቶ መረጣችሁ። 16ስለዚህ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙት፤ ከእንግዲህም ወዲያ ዐንገተ ደንዳና አትሁኑ። 17አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ ታላቅ አምላክ፣ ኀያልና የሚያስፈራ፣ አድልዎ የማያደርግ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና። 18እርሱ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች ይፈርዳል፤ መጻተኛውንም ምግብና ልብስ በመስጠት ይወድዳል። 19ስለዚህ እናንተም በግብጽ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛን ውደዱ። 20አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ አምልከውም፤ ከርሱም ጋራ ተጣበቅ፤ በስሙም ማል። 21እርሱ ውዳሴህ ነው፤ በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን፣ እነዚያን ታላላቅና አስፈሪ ነገሮች ያደረገልህ አምላክህ ነው። 22አባቶችህ ወደ ግብጽ ሲወርዱ ሰባ ነበሩ፤ አሁን ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰማይ ከዋክብት አብዝቶሃል።

Currently Selected:

ዘዳግም 10: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ