አሞጽ 6
6
ተዘልላ ላለችው እስራኤል የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1በጽዮን ተዘልላችሁ የምትቀመጡ፣
በሰማርያ ተራራ ያለ ሥጋት የምትኖሩ፣
የእስራኤልም ሕዝብ ለርዳታ ወደ እናንተ የሚመጡባችሁ፣
እናንተ የአሕዛብ አለቆች ሆይ፤ ወዮላችሁ!
2ወደ ካልኔ ሂዱ፤ እርሱንም ተመልከቱ፤
ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤
ወደ ፍልስጥኤም ከተማ ወደ ጋትም ውረዱ፤
እነዚህ ከሁለቱ መንግሥታታችሁ ይሻላሉን?
የምድራቸውስ ስፋት ከእናንተ ይበልጣልን?
3ክፉውን ቀን ለምታርቁ፣
የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ ወዮላችሁ!
4በዝኆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ ለምትተኙ፤
በድንክ ዐልጋችሁ ላይ ለምትዝናኑ፣
ከበጎች መንጋ ጠቦትን፣
ከሠቡትም ጥጃን ለምትበሉ፤
5ባልተቃኘ በገና እንደ ዳዊት ለምትዘፍኑ፣
በሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ለምትሹ፣
6በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣
ምርጥ ሽቱም ለምትቀቡ፣
ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ወዮላችሁ!
7ስለዚህ እናንተ በመጀመሪያ በምርኮ ከሚወሰዱት መካከል ናችሁ፤
መፈንጠዛችሁና መዝናናታችሁም ያበቃል።
እግዚአብሔር የእስራኤልን ትዕቢት ይጸየፋል
8ጌታ እግዚአብሔር
“የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፤
ምሽጎቹንም ጠልቻለሁ፤
ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣
አሳልፌ እሰጣለሁ”
ሲል በራሱ ምሏል፤ ይላል የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር።
9በአንድ ቤት ውስጥ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም ይሞታሉ። 10በድኖቹንም ከቤት አውጥቶ ማቃጠል ያለበት አንድ ዘመድ መጥቶ ተደብቆ ያለውን ሰው፣ “ከአንተ ጋራ የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ሲለው፣ እርሱም “የለም” ይለዋል፤ ከዚያም በኋላ፣ “ዝም በል፤ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አይገባንም” ይለዋል።
11እነሆ፤ እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጥቷልና፤
ታላላቅ ቤቶችን ያወድማቸዋል፤
ትንንሾቹንም ያደቅቃቸዋል።
12ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን?
ሰውስ እዚያ ላይ በበሬ ያርሳልን?
እናንተ ግን ፍትሕን ወደ መርዝነት፣
የጽድቅንም ፍሬ ወደ መራራነት ለወጣችሁ።
13እናንተ ሎዶባርን#6፥13 ትርጕሙ ምንም ማለት ነው። በማሸነፋችሁ ደስ ያላችሁ፣
“ቃርናይምን#6፥13 ቃርናይም ትርጕሙ ቀንዶች ማለት ነው፤ ቀንድ የጥንካሬ ምልክት ነው። በራሳችን ብርታት ይዘናል” የምትሉ።
14የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣
“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እነሆ፤ እኔ ከሐማት መግቢያ#6፥14 ወይም ከመግቢያው ጀምሮ እስከ ዓረባ ሸለቆ ድረስ፣
የሚያስጨንቃችሁን ሕዝብ፣ በእናንተ
ላይ አስነሣለሁ።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.