አሞጽ 5
5
የእስራኤል ሕዝብ ለንስሓ መጠራት
1የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ የምደረድረውን ይህን የሙሾ ቃል ስሙ፤
2“ድንግሊቱ እስራኤል ወደቀች፤
ከእንግዲህም አትነሣም፤
በገዛ ምድሯ ተጣለች፤
የሚያነሣትም የለም።”
3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“አንድ ሺሕ ብርቱዎችን ለእስራኤል የምታዘምት ከተማ፣
አንድ መቶ ብቻ ይቀሯታል፤
አንድ መቶ ብርቱዎችን የምታዘምተውም፣
ዐሥር ብቻ ይቀሯታል።”
4 እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላል፤
“እኔን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
5ቤቴልን አትፈልጉ፤
ወደ ጌልገላ አትሂዱ፤
ወደ ቤርሳቤህም አትሻገሩ፤
ጌልገላ በርግጥ ትማረካለች፤
ቤቴልም እንዳልነበረች#5፥5 በዕብራይስጡ አቨን የሚል ሲሆን ቤተ አቨን ለሚለው የሚያመላክት ነው (ቤቴል ለሚለው ቃል በሚያዋርድ መልኩ ለመጥራት የሚውል ነው)። ሆሴ 4፥15 ይመ። ትሆናለችና።”
6 እግዚአብሔርን ፈልጉ፤
በሕይወትም ትኖራላችሁ፤
አለዚያ እንደ እሳት የዮሴፍን ቤት ያወድማል፤
እሳቱም ቤቴልን ይበላል፤ የሚያጠፋውም የለም።
7እናንተ ፍትሕን ወደ መራርነት የምትለውጡ፣
ጽድቅንም ወደ ምድር የምትጥሉ ወዮላችሁ!
8ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮንን የሠራ፣
ጨለማውን ወደ ንጋት ብርሃን የሚለውጥ፣
ቀኑን አጨልሞ ሌሊት የሚያደርግ፣
የባሕሩንም ውሃ ጠርቶ፣
በገጸ ምድር ላይ የሚያፈስስ፣
ስሙ እግዚአብሔር ነው፤
9እርሱ በብርቱው ላይ ድንገተኛ ጥፋትን፣
በተመሸገውም ከተማ ላይ ውድመትን ያመጣል።
10እናንተ በፍርድ አደባባይ
የሚገሥጻችሁን ትጠላላችሁ፤ እውነት የሚናገረውንም ትንቃላችሁ።
11እናንተ ድኻውን ትረግጣላችሁ፤
እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤
ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣
በውስጡ ግን አትኖሩም፤
ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣
የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤
12ኀጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደ ሆነ፣
በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና።
ጻድቁን ትጨቍናላችሁ፤
ጕቦም ትቀበላላችሁ፤
በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።
13ስለዚህ አስተዋይ ሰው በእንዲህ ያለ ጊዜ ዝም ይላል፤
ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና።
14በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፣
መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤
ከዚያ በኋላ እንደ ተናገራችሁት፣
የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሆናል።
15ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤
በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤
ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር፣
ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።
16ስለዚህ ጌታ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በየመንገዱ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤
በአደባባዩም የሥቃይ ጩኸት ይሆናል፤
ገበሬዎች ለልቅሶ፣
አልቃሾችም ለዋይታ ይጠራሉ።
17በየወይኑ ዕርሻ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤
እኔ በመካከላችሁ ዐልፋለሁና፤”
ይላል እግዚአብሔር።
የእግዚአብሔር ቀን
18የእግዚአብሔርን ቀን ለምትሹ፣
ለእናንተ ወዮላችሁ!
የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትሻላችሁ?
ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።
19ይህ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሲሸሽ፣
ድብ እንደሚያጋጥመው፣
ወደ ቤቱም ገብቶ፣ እጁን በግድግዳው
ላይ ሲያሳርፍ፣
እባብ እንደሚነድፈው ነው።
20የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ፣
የብርሃን ጸዳል የሌለው ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?
21“ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤
ጠልቼውማለሁ፤ ጉባኤዎቻችሁ ደስ አያሰኙኝም።
22የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ብታቀርቡልኝም፣
እኔ አልቀበለውም፤
ከሠቡ እንስሶቻችሁ የኅብረት መሥዋዕት#5፥22 የሰላም መሥዋዕት በመባል የሚታወቀው ነው። ብታቀርቡልኝም፣
እኔ አልመለከተውም።
23የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤
የበገናህንም ዜማ አልሰማም።
24ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣
ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።
25“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣
መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን?
26ይልቁንም ለራሳችሁ የሠራችኋቸውን፣
የንጉሣችሁን የሲኩትን ጣዖታት፣ የኮከብ አምላክ የሆነውን የሪፋን አማልክት አንሥታችሁ ተሸከማችሁ።#5፥26 ወይም ከፍ ከፍ ታደርጋላችሁ ሰብዓ ሊቃናት የሞሌክን ቤተ ጣዖት እንዲሁም የአምላካችሁን የሬፋንን ከዋክብት ከፍ አደረጋችሁ ይላሉ።
27ስለዚህ ከደማስቆ ማዶ እንድትጋዙ አደርጋለሁ፤”
ይላል ስሙ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር የሆነ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.