አሞጽ 2
2
1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ስለ ሦስቱ የሞዓብ ኀጢአት፣
ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤
የኤዶምን ንጉሥ ዐጥንት፣
ዐመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሏልና፤
2የቂርዮትን ምሽጎች#2፥2 ወይም ከተሞቿ እንዲበላ፣
በሞዓብ ላይ እሳት እሰድዳለሁ፤
ሞዓብ በጦርነት ጩኸትና በመለከት ድምፅ መኻል፣
በታላቅ ሁካታ ውስጥ ይሞታል።
3ገዥዋን እደመስሳለሁ፣
አለቆቿንም ሁሉ ከንጉሧ ጋራ እገድላለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ስለ ሦስቱ የይሁዳ ኀጢአት፣
ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤
የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋል፤
ትእዛዙንም አልጠበቁምና፤
አባቶቻቸው በተከተሏቸው#2፥4 ወይም በውሸት አማልክት፣
በሐሰት#2፥4 ወይም ውሸት አማልክት በመመራት ስተዋልና።
5የኢየሩሳሌምን ምሽጎች እንዲበላ፣
በይሁዳ ላይ እሳት እሰድዳለሁ።”
በእስራኤል ላይ የተሰጠ ፍርድ
6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣
ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤
ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣
ድኻውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና።
7የችግረኞችን ራስ፣
በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤
ፍትሕንም ከጭቍኖች ይነጥቃሉ፤
አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋራ ይተኛሉ፤
እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ።
8በመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ፣
በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤
በአምላካቸው ቤት፣
በመቀጫነት የተወሰደውን የወይን ጠጅ ይጠጣሉ።
9“ቁመቱ እንደ ዝግባ፣
ጥንካሬውም እንደ ወርካ ዛፍ የነበረ ቢሆንም፣
አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁት፣
ከላይ ፍሬውን፣
ከታችም ሥሩን አጠፋሁ።
10የአሞራውያንን ምድር ልሰጣችሁ፣
ከግብጽ አወጣኋችሁ፤
አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መራኋችሁ።
11“ደግሞም ነቢያትን ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል፣
ናዝራውያንንም ከጕልማሶቻችሁ መካከል አስነሣሁ፤
የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ ይህ እውነት አይደለምን?”
ይላል እግዚአብሔር።
12“እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤
ነቢያቱንም ትንቢት እንዳይናገሩ አዘዛችኋቸው።
13“እነሆ፤ በእህል የተሞላ ጋሪ እንደሚያደቅቅ፣
እኔም አደቅቃችኋለሁ።
14ፈጣኑ አያመልጥም፤
ብርቱውንም ብርታቱ አይረዳውም፤
ኀያሉም ነፍሱን አያድንም።
15ቀስተኛው በቦታው ጸንቶ አይቆምም፤
ፈጣኑም ተዋጊ ሮጦ አያመልጥም፤
ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም።
16ጐበዞቹ ተዋጊዎች እንኳ፣
በዚያ ቀን ዕራቍታቸውን ይሸሻሉ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.