ሐዋርያት ሥራ 9:23-43

ሐዋርያት ሥራ 9:23-43 NASV

ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤ ሳውል ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤ የርሱ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት በከተማዪቱ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት። ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋራ ለመቀላቀል ሞከረ፤ እነርሱ ግን በርግጥ ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት። ይሁን እንጂ በርናባስ ወስዶ ወደ ሐዋርያት አመጣው፤ ሳውልም በጕዞው ላይ ሳለ ጌታን እንዴት እንዳየው፣ ጌታም እንዴት እንደ ተናገረው እንዲሁም በደማስቆ በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። ስለዚህ ሳውል ዐብሯቸው ተቀመጠ፤ በኢየሩሳሌምም በመዘዋወር በጌታ ስም በድፍረት ይናገር ነበር። ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋራ እየተነጋገረ ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ጥረት ያደርጉ ነበር። ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሳርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ሰደዱት። በዚህ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር ጀመረች፤ ተጠናከረችም። ደግሞም ጌታን በመፍራት እየተመላለሰችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቍጥር እየበዛች ሄደች። ጴጥሮስም ከአገር ወደ አገር በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ በልዳ የሚኖሩትን ቅዱሳን ለመጐብኘት ወረደ። በዚያም ኤንያ የተባለ፣ ስምንት ዓመት የዐልጋ ቍራኛ የነበረ አንድ ሽባ ሰው አገኘ። ጴጥሮስም፣ “ኤንያ ሆይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣና መኝታህን አንጥፍ” አለው። ኤንያም ወዲያውኑ ብድግ አለ። በልዳና በሰሮና የሚኖሩትም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ። በኢዮጴ ጣቢታ የተባለች አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጓሜ ዶርቃ ማለት ነው። እርሷም ዘወትር በትጋት በጎ ነገር እያደረገችና ድኾችን እየረዳች ትኖር ነበር። በዚያ ጊዜም ታምማ ሞተች፤ ሰዎችም አስከሬኗን ዐጥበው በሰገነት ላይ ባለው ክፍል አስቀመጡት። ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለ ነበረች፣ ደቀ መዛሙርትም ጴጥሮስ በልዳ መሆኑን በሰሙ ጊዜ ሁለት ሰዎች ልከው፣ “እባክህ ፈጥነህ ወደ እኛ ና!” ሲሉ ለመኑት። ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋራ ሄደ፤ እዚያ በደረሰ ጊዜም ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍል አወጡት። መበለቶቹም ሁሉ ዶርቃ ከእነርሱ ጋራ በነበረችበት ጊዜ ያደረገቻቸውን ቀሚሶችና ልብሶች እያሳዩት ዙሪያውን ከብበው ያለቅሱ ነበር። ጴጥሮስም ሁሉንም ከክፍሉ አስወጥቶ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ፣ “ጣቢታ፤ ተነሺ” አለ። እርሷም ዐይኗን ገለጠች፤ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ቀና ብላ ተቀመጠች፤ እርሱም እጇን ይዞ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶቹንም ጠርቶ ከነሕይወቷ አስረከባቸው። ይህም ነገር በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። ጴጥሮስም ስምዖን ከተባለ ከአንድ ቍርበት ፋቂ ጋራ በኢዮጴ ብዙ ቀን ተቀመጠ።