ሐዋርያት ሥራ 20
20
ወደ መቄዶንያና ወደ ግሪክ ጕዞ
1ሁከቱም እንደ በረደ፣ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርትን አስጠርቶ መከራቸው፤ ተሰናብቷቸውም ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ተነሣ። 2ባለፈባቸውም ስፍራዎች ሕዝቡን በብዙ ቃል እየመከረ ግሪክ አገር ደረሰ፤ 3በዚያም ሦስት ወር ተቀመጠ። ወደ ሶርያ በመርከብ ለመሄድ ሲዘጋጅም አይሁድ አሢረውበት ስለ ነበር፣ በመቄዶንያ በኩል አድርጎ ለመመለስ ወሰነ። 4የጳይሮስ ልጅ የቤርያው ሱሲጴጥሮስ፣ የተሰሎንቄዎቹ አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ፣ የደርቤኑ ጋይዮስ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ እንዲሁም ጢሞቴዎስ ዐብረውት ሄዱ። 5እነዚህም ሰዎች ወደ ፊት ቀድመውን በጢሮአዳ ጠበቁን። 6እኛ ግን የቂጣ በዓል ካለፈ በኋላ፣ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሣን፤ ከዐምስት ቀንም በኋላ ከሌሎቹ ጋራ በጢሮአዳ ተገናኘን፤ በዚያም ሰባት ቀን ተቀመጥን።
አውጤኪስ በጢሮአዳ ከሞት ተነሣ
7በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቍረስ ተሰብስበን ሳለን፣ ጳውሎስ በማግስቱም ለመሄድ ስላሰበ፣ ከእነርሱ ጋራ ይነጋገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አራዘመ። 8በተሰበሰብንበትም ሰገነት ላይ ብዙ መብራት ነበር። 9አውጤኪስ የተባለ አንድ ጐበዝም በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አለውና ጭልጥ ብሎ ተኛ፤ ከሦስተኛውም ፎቅ ቍልቍል ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት። 10ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ተጋድሞ ዐቀፈውና፣ “ሕይወቱ በውስጡ ስላለች ሁከት አትፍጠሩ!” አላቸው። 11ተመልሶም እንደ ገና ወደ ፎቁ ወጣ፤ እንጀራውንም ቈርሶ በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ብዙ ከተናገረ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። 12ሰዎችም ያን ጐበዝ ሕያው ሆኖ ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ።
ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች ተሰናበተ
13እኛ ግን ጳውሎስን ለመቀበል ቀድመን ወደ መርከቡ ሄድን፤ ከዚያም በመርከብ ወደ አሶን ተጓዝን፤ ይህን ያደረግነውም ጳውሎስ በየብስ በእግሩ ሊሄድ ስላሰበ ነበር። 14በአሶን ከተገናኘንም በኋላ፣ ተቀብለነው ዐብረን በመርከብ ወደ ሚጢሊኒ ሄድን። 15በማግስቱም በመርከብ ተጕዘን ከኪዩ ደሴት ትይዩ ደረስን። በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞን ተሻገርን፤ በማግስቱም ሚሊጢን ደረስን። 16ጳውሎስም በእስያ አውራጃ ብዙ መቈየት ስላልፈለገ፣ ወደ ኤፌሶን ሳይገባ ዐልፎ ለመሄድ ወሰነ፤ ቢቻል በዓለ ዐምሳን በኢየሩሳሌም ለመዋል ቸኵሎ ነበርና።
17ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ሰው ልኮ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሽማግሌዎች አስጠራ። 18በመጡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ወደ እስያ አውራጃ ከገባሁባት ከመጀመሪያዋ ዕለት አንሥቶ ዘወትር ከእናንተ ጋራ እንዴት እንደ ኖርሁ ታውቃላችሁ። 19ምንም እንኳ ከአይሁድ ሤራ የተነሣ መከራ ቢያደርሱብኝም፣ ጌታን በታላቅ ትሕትናና በእንባ ከማገልገል አልተቈጠብሁም፤ 20በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም። 21በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ፣ ለአይሁድም ለግሪክ ሰዎችም አጥብቄ መስክሬላቸዋለሁ።
22“አሁንም እዚያ ስደርስ የሚደርስብኝን ባላውቅም፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው። 23ነገር ግን በምሄድባቸው ከተሞች ሁሉ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። 24ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።
25“አሁንም ቢሆን፣ በመካከላችሁ ተዘዋውሬ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ፣ እናንተ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲያ ፊቴን እንደማታዩ ዐውቃለሁ። 26ስለዚህ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኔን በዚህች ቀን እመሰክርላችኋለሁ፤ 27የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመግለጽ የተቈጠብሁበት ጊዜ የለምና። 28ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስ ቆጶሳት#20፥28 ወይም በትውፊት “ጳጳሳት” ይባል ነበር። አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን#20፥28 ብዙ የጥንት ቅጆች የጌታን ይላሉ። ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ። 29እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሠርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ። 30ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ። 31ስለዚህ ተጠንቀቁ! ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን ምን ያህል ሳላቋርጥ በእንባ እያንዳንዳችሁን እንደ መከርኋችሁ አስታውሱ።
32“አሁንም ለእግዚአብሔር፣ እንዲሁም ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል ዐደራ እሰጣችኋለሁ። 33የማንንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤ 34እነዚህ እጆቼ ለእኔና ከእኔ ጋራ ላሉት በሚያስፈልገን ነገር እንዳገለገሉን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 35በጕልበታችን ደክመን ችግረኞችን መርዳት እንዳለብን ባደረግሁት ሁሉ አሳይቻችኋለሁ፤ ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ምስጉን ነው’ ያለውን የጌታ የኢየሱስን ቃል እናስታውስ።”
36ይህን ካለ በኋላ፣ ተንበርክኮ ከሁሉም ጋራ ጸለየ። 37ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም ዐንገቱን ዐቅፈው ሳሙት። 38ከሁሉም በላይ ልባቸውን የነካው፣ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቱን እንደማያዩ የተናገራቸው ቃል ነበር። ከዚያም እስከ መርከቡ ድረስ ሸኙት።
Currently Selected:
ሐዋርያት ሥራ 20: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.