2 ጢሞቴዎስ 4:9-22

2 ጢሞቴዎስ 4:9-22 NASV

በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ዴማስ ይህን ዓለም ወድዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዷልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤ ከእኔ ጋራ ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋራ ይዘኸው ና። ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ። ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖስ፣ ጥቅልል መጻሕፍቱን፣ በተለይም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ። አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጕዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል። መልእክታችንን እጅግ ተቃውሟልና፤ አንተም ከርሱ ተጠንቀቅ። በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው። ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳም መንጋጋ አዳነኝ። ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። ለጵርስቅላና ለአቂላ፣ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቷል፤ ጥሮፊሞስም ስለ ታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ። ከክረምት በፊት እዚህ ለመምጣት የተቻለህን አድርግ። ኤውግሎስና ጱዴስ እንዲሁም ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ጌታ ከመንፈስህ ጋራ ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን።