2 ሳሙኤል 21
21
የገባዖናውያን ብቀላ
1በዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፣ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ።
2ንጉሡ ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፣ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤ 3ዳዊትም ገባዖናውያንን፣ “ምን ላድርግላችሁ? የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተስረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው።
4ገባዖናውያንም፣ “ከሳኦልም ሆነ ከቤተ ሰቡ ብር ወይም ወርቅ የመጠየቅ መብት የለንም፤ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት።
ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
5እነርሱም ንጉሡን፣ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው 6ከርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት።
ስለዚህ ንጉሡ፣ “ዕሺ እሰጣችኋለሁ” አለ።
7ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በእግዚአብሔር ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፣ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን ከሞት አተረፈ። 8ነገር ግን ንጉሡ፣ የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን፤ የሳኦል ልጅ ሜሮብ#21፥8 ሁለት የዕብራይስጥ ቅጆች፤ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ (እንዲሁም 1ሳሙ 18፥19 ይመ)፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥና የሰብዓ ሊቃናት ቅጆች ግን፣ ሜልኮል ይላሉ። ለመሓላታዊው ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደችለትን ዐምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤ 9ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ የተገደሉትም በመከሩ ወራት የመጀመሪያ ቀኖች፣ የገብስ ዐጨዳ በተጀመረበት ዕለት ነበር።
10የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፣ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከ ወረደ ጊዜ ድረስ፣ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤ 11የሳኦል ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፣ 12ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ወሰደ፤ የኢያቢስ ገዦች፣ ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ ከገደሉ በኋላ እነርሱን ከሰቀሉት ከቤትሳን አደባባይ በድብቅ ወስደዋቸው ነበር። 13ዳዊትም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አመጣ፤ እንዲሁም የእነዚያን የተገደሉትን ሰዎች ዐፅም ሰበሰቡ።
14የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
በፍልስጥኤማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት
21፥15-22 ተጓ ምብ – 1ዜና 20፥4-8
15እንደ ገና በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተደረገ። ዳዊትም ከሰዎቹ ጋራ ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወረደ፤ በዚያም ደከመው። 16ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነ ይሽቢብኖብ የተባለ፣ የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል#21፥16 3.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። የሚመዝንና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ሰው ነበረ፤ እርሱም ዳዊትን ለመግደል ዐሰበ። 17የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም ወግቶ ገደለው። ከዚያም የዳዊት ሰዎች፣ “የእስራኤል መብራት እንዳይጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋራ ወደ ጦርነት መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት።
18ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ሌላ ጦርነት ተደረገ። በዚያ ጊዜም ኩሳታዊው ሴቦካይ፣ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነውን፣ ሳፍን ገደለው።
19ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ በተደረገ ሌላ ጦርነትም፣ የቤተ ልሔሙ የዓሬዓርጊም ልጅ ኤልያናን#21፥19 1ዜና 20፥5 ይመ፤ ዕብራይስጡ ያዔር ኦረጊም ይለዋል።፣ የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጋት ሰው የጎልያድን#21፥19 1ዜና 20፥5 ይመ፤ ወንድም ገደለው።
20እንደ ገና ጋት ላይ በተደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች በአጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም ዘር ነበረ። 21እርሱም እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፣ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው።
22እነዚህ አራቱ በጋት የራፋይም ዘሮች የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.