2 ሳሙኤል 12:1-10

2 ሳሙኤል 12:1-10 NASV

እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ባለጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ ዐብራውም ከልጆቹ ጋራ አደገች፤ ዐብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደ ገዛ ልጁ ነበረች። “ወደ ባለጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፣ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለልኸው ስለ ምንድን ነው? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም፤ እኔን አቃልለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የኬጢያዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና።’