ወዳጆች ሆይ፤ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው። ሁለቱንም መልእክቶች የጻፍሁላችሁ ቅን ልቡናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል፣ እንዲሁም በሐዋርያት አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስቡ ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞቶቻቸውን የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሰማያት ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረው እንደሚኖሩ፣ መሬትም በውሃ መካከልና በውሃም እንደ ተሠራች ሆነ ብለው ይክዳሉ፤ በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። በዚያው ቃል ደግሞ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል። ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺሕ ዓመት፣ ሺሕ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል። እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያ ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።
2 ጴጥሮስ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ጴጥሮስ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ጴጥሮስ 3:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች