2 ነገሥት 25
25
1በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መላ ሰራዊቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ፤ ከከተማዪቱ ቅጥር ውጭ ሰፈረ፤ ዙሪያውንም በሙሉ በዕርድ ከበባት። 2ከተማዪቱም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች።
3በአራተኛው#25፥3 ኤር 52፥6 ይመ ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ውስጥ የተከሠተው ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚቀምሰው ዐጣ። 4ምንም እንኳ ባቢሎናውያን#25፥4 ወይም ከለዳውያን በዚህና በቍጥር 13፣ 25 እንዲሁም በ26 ላይ ይገኛል። ከተማዪቱን እንደ ከበቧት ቢሆንም የከተማዪቱ ቅጥር ተጣሰ፤ ሰራዊቱም ሁሉ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ባሉት በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በዓረባ በር ዐልፎ በሌሊት ሸሸ፤ ሽሽቱም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ#25፥4 ወይም፣ በዓረባም ነበር። 5ይሁን እንጂ የባቢሎናውያንም#25፥5 ወይም ከለዳውያን በዚህም ሆነ በቍጥር 10 እና 24 ላይ፣ ሰራዊት ንጉሡን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ደረሱበት። ወታደሮቹም ሁሉ ተለይተውት ተበታትነው ሳለ 6ንጉሡን ያዙት።
በዚያ ጊዜ ሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ በዚያም የባቢሎን ንጉሥ ፈረደበት። 7ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየም ወንዶች ልጆቹን ገደሉበት፤ ከዚያም ሁለት ዐይኖቹን በማውጣት በናስ ሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።
8የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፣ በዐምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 9የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥቱን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እያንዳንዱንም ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ። 10በክብር ዘቡ አዛዥ የተመራው መላው የባቢሎን ሰራዊትም በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበረውን ቅጥር አፈረሰው። 11የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዘረዳን ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው። 12ሆኖም የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሌሎች የምድሪቱን ድኾች፣ ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።
13ባቢሎናውያን የናስ ዐምዶቹን፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩትን ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 14እንዲሁም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ጭልፋዎቹን፣ በአጠቃላይም ከናስ የተሠሩትን የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ። 15የክብር ዘቡ አዛዥም ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ጥናዎችና የመርጫ ወጭቶችን ወሰደ።
16ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ ብሎ ከናስ ያሠራቸው ሁለት ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፤ ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር። 17እያንዳንዱም ዐምድ ከፍታው ዐሥራ ስምንት ክንድ#25፥17 8.1 ሜትር ያህል ነው። ሲሆን፣ የናስ ጕልላት ነበረው፤ የጕልላቱ ርዝመት ሦስት ክንድ#25፥17 1.4 ሜትር ያህል ነው። ሆኖ፣ ዙሪያውን በሙሉ የናስ መርበብና የሮማን ፍሬዎች ቅርጽ ነበረው፤ ሌላውም ዐምድ ከነቅርጾቹ ከዚሁ ጋራ ተመሳሳይ ነበር።
18የክብር ዘበኞቹ አዛዥም ሊቀ ካህኑን ሠራያን፣ በማዕርግ ከርሱ ቀጥሎ ያለውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች እስረኛ አድርጎ ወሰዳቸው። 19እስከዚያች ጊዜ ድረስ በከተማዪቱ ውስጥ ከቀሩትም የተዋጊዎቹን አለቃና ዐምስት የንጉሡን አማካሪዎች ወሰዳቸው። ደግሞም የአገሩን ሕዝብ ለውትድርና የሚመለምለውን ዋና የጦር አለቃ የነበረውን ጸሓፊውንና በከተማዪቱ ውስጥ የተገኙትን የጸሓፊውን ስድሳ ሰዎች ወሰዳቸው። 20የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 21ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ውስጥ አስገደላቸው።
ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ።
22የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የሳፋን ልጅ የሆነውን የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስን እዚያው በቀረው በይሁዳ ሕዝብ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23መላው የሰራዊቱ ጦር አለቆችና ሰዎቻቸው የባቢሎን ንጉሥ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ጎዶልያስን መሾሙን ሲሰሙ፣ እርሱ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ እነርሱም የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋዊው የተንሑሜት ልጅ ሠራያ የማዕካታዊው ልጅ ያእዛንያና ሰዎቻቸው ነበሩ። 24ጎዶልያስም፣ “የባቢሎናውያንን ሹማምት አትፍሩ፤ እዚሁ አገር ኑሩ፤ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ ሁሉም ነገር ይሳካላችኋል” ሲል ይህንኑ በቃለ መሐላ አረጋገጠላቸው።
25ነገር ግን በሰባተኛው ወር ንጉሣዊ ዝርያ የነበረው የኤሊሳማ የልጅ ልጅ የሆነው የናታንያ ልጅ እስማኤል ዐሥር ሰዎች ይዞ መጥቶ ጎዶልያስንና በምጽጳ ዐብረውት የነበሩትን የይሁዳን ሰዎችና ባቢሎናውያንን ገደለ። 26ባቢሎናውያንን ከመፍራታቸው የተነሣም ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ከሰራዊቱ የጦር አለቆች ጋራ ወደ ግብጽ ሸሹ።
ዮአኪን ከእስራት ተፈታ
25፥27-30 ተጓ ምብ – ኤር 52፥31-34
27የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን ዮርማሮዴክ በባቢሎን በነገሠ በዓመቱ ዮአኪንን ከወህኒ ፈታው። 28በመልካምም ቃል አናገረው፤ ከርሱም ጋራ በባቢሎን በምርኮ ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ባለ የክብር ቦታ አስቀመጠው። 29ዮአኪንም የእስር ቤት ልብሱን ጣለ፤ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማእድ ዘወትር ይመገብ ነበር፤ 30ንጉሡም ለዮአኪን እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የዕለት ቀለቡን ይሰጠው ነበር።
Currently Selected:
2 ነገሥት 25: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.