2 ነገሥት 24
24
1በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ምድሪቱን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ገበረለት፤ ከዚያ በኋላ ግን ሐሳቡን ለውጦ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ። 2እግዚአብሔርም በኢዮአቄም ላይ ባቢሎናውያን#24፥2 ወይም ከለዳውያን፣ ሶርያውያን፣ ሞዓባውያንና አሞናውያን አደጋ ጣዮችን ላከበት፤ በአገልጋዮቹ በነቢያቱ አማካይነት በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ይሁዳን ያጠፉ ዘንድ እነዚህን ላከ። 3ከፊቱ ያርቃቸው ዘንድ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በይሁዳ ላይ በትክክል ሊፈጸሙ ችለዋል፤ ይህም ምናሴ ስለ ሠራው ኀጢአትና ስለ ፈጸመውም ሁሉ፣ 4እንዲሁም ንጹሕ ደም ስላፈሰሰ ነው። ኢየሩሳሌምም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ፤ እግዚአብሔር ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።
5በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 6ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ዮአኪንም በምትኩ ነገሠ።
7የባቢሎንም ንጉሥ ከግብጽ ደረቅ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ የነበረውን ግዛቱን ሁሉ ወስዶበት ስለ ነበር፣ የግብጽ ንጉሥ ከአገሩ ዳግም ለዘመቻ አልወጣም።
የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን
24፥8-17 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥9-10
8ዮአኪን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ። እናቱ ኔስታ ትባላለች፤ እርሷም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች። 9አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10በዚያ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ጦር አለቆች ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መጥተው ከበቧት፤ 11የጦር አለቆቹ ከበባ በሚያደርጉበትም ሰዓት ንጉሥ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ከተማዪቱ መጣ። 12የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን፣ እናቱ፣ የክብር አጃቢዎቹ፣ መሳፍንቱና ሹማምቱ ሁሉ እጃቸውን ለባቢሎን ንጉሥ ሰጡ።
የባቢሎን ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው። 13እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ አጋዘ፤ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያሠራቸውንም የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ። 14ደግሞም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ እንዳለ የጦር አለቆቹንና ተዋጊዎቹን በሙሉ፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ቀጥቃጮችን ሁሉ ጨምሮ በአጠቃላይ ዐሥር ሺሕ ሰው በምርኮ ወደ አገሩ ወሰደ። በዚያ የቀሩት የመጨረሻዎቹ ያገሪቱ ድኾች ብቻ ነበሩ።
15ናቡከደነፆር ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ እንዲሁም የንጉሡን እናት፣ ሚስቶቹን፣ ሹማምቱና በአገር የታወቁትን ታላላቅ ሰዎችም ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ወሰደ። 16ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ በአጠቃላይ ብርቱ የሆኑትንና ለጦርነት ብቃት ያላቸውን ሰባት ሺሕ ተዋጊዎች፣ አንድ ሺሕ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ቀጥቃጮችን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ። 17ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያን በምትኩ አነገሠው፤ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።
የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ
24፥18-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥11-16፤ ኤር 52፥1-3
18ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። የእናቱም ስም አሚጣል ነበረ፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 19ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 20እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው።
የኢየሩሳሌም መውደቅ
25፥1-12 ተጓ ምብ – ኤር 39፥1-10
25፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥17-20፤ ኤር 52፥27
25፥22-26 ተጓ ምብ – ኤር 40፥7-9፤ 41፥1-3፤ 41፥16-18
በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 24: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.