2 ነገሥት 19

19
ኢየሩሳሌም ከጠላት እጅ እንደምትድን አስቀድሞ መነገሩ
19፥1-13 ተጓ ምብ – ኢሳ 37፥1-13
1ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። 2ከዚያም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፣ ጸሓፊውን ሳምናስንና ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። 3እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ልጆች ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኗል። 4ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።’ ”
5የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤ 6ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር። 7እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”
8የጦር አዛዡም የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ትቶ መሄዱን ሲሰማ ተመለሰ፤ ንጉሡም ልብናን ሲወጋ አገኘው።
9ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ#19፥9 ከአባይ ወንዝ በስተሰሜን ያለ አካባቢን የሚያመላክት ነው። ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤ 10“ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልልህ። 11እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 12የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን? 13የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?”
የሕዝቅያስ ጸሎት
19፥14-19 ተጓ ምብ – ኢሳ 37፥14-20
14ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል። 16አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈትና እይ፤ ሰናክሬም ሕያው እግዚአብሔርን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ።
17እግዚአብሔር ሆይ፤ የአሦር ነገሥታት እውነትም እነዚህን አሕዛብንና ምድራቸውን አጥፍተዋል። 18አማልክታቸውን በእሳት ውስጥ ጥለው አቃጥለዋቸዋል፤ በሰው እጅ የተሠሩ ዕንጨትና ድንጋይ ብቻ እንጂ አማልክት አልነበሩምና። 19አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆንህን ያውቁ ዘንድ፣ ከእጁ አድነን።”
ኢሳይያስ ስለ ሰናክሬም መውደቅ ትንቢት ተናገረ
19፥20-37 ተጓ ምብ – ኢሳ 37፥21-38
19፥35-37 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥20-21
20ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በአሦር ንጉሥ በሰናክሬም ላይ ወደ እኔ ያቀረብኸውን ልመና ሰምቻለሁ’ 21እንግዲህ እግዚአብሔር በርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤
“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣
ንቃሃለች፤ ታቃልልሃለችም፤
የኢየሩሳሌም ልጅ፣
አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።
22ለመሆኑ የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?
ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው?
ዐይንህንስ በኵራት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?
በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እንዴ?
23በመልእክተኞችህ በኩል፣
በጌታ ላይ የስድብ ቃል ተናገርህ፤
እንዲህም አልህ፤
“በሠረገሎቼ ብዛት፣
የተራሮችንም ከፍታ፣
የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤
ረዣዥም ዝግባዎችን፣
የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤
እጅግ ወደራቁት፣
እጅግ ውብ ወደሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ።
24በባዕድ ምድር የውሃ ጕድጓዶችን ቈፈርሁ፤
በዚያም ውሃ ጠጣሁ።
የግብጽን ምንጮች ሁሉ፣
በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።”
25“ ‘ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣
አልሰማህምን?
ጥንትም እንዳቀድሁት፣
አሁን ግን እንዲፈጸም አደረግሁት፤
ይህም የተመሸጉትን ከተሞች፣
አንተ የድንጋይ ክምር ማድረግህ ነው።
26የሚኖሩባቸውም ሰዎች ኀይላቸው ተሟጥጦ ዐልቋል፤
ደንግጠውም የኀፍረት ማቅ ለብሰዋል፤
ሜዳ ላይ እንደ በቀለ ተክል፣
ገና እንዳልጠነከረ የቡቃያ ሥር፣
በቤት ጣራ ላይ በቅሎ፣
ገና ሳያድግ እንደ ጠወለገ ሣርም ሆነዋል።
27“ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣
መቼ እንደምትመጣና መቼ እንደምትሄድ፣
በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደምትነሣሣ ዐውቃለሁ።
28በእኔ ላይ በቍጣ ስለ ተነሣሣህ፣
እብሪትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣
ስናጋዬን በአፍንጫህ አደርጋለሁ፤
ልጓሜን በአፍህ አስገባለሁ፤
በመጣህበትም መንገድ
እንድትመለስ አደርግሃለሁ።’
29“ሕዝቅያስ ሆይ፤ ምልክቱ ይህ ነው፤
“በዚህ ዓመት በገዛ እጁ የበቀለውን፣
በሚመጣው ዓመት ደግሞ የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤
በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤
ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።
30አሁንም ከይሁዳ ቤት የተረፉት፣
ሥራቸውን ወደ ታች ይሰድዳሉ፤ ወደ ላይም ፍሬ ያፈራሉ።
31ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣
የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና።
የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።
32“ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤
“ ‘ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤
ፍላጻም አይወረውርባትም፤
ጋሻ አንግቦ አይቀርብም፤
በዐፈርም ቍልል አይከብባትም።
33በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤
ወደዚህች ከተማም አይገባም’
ይላል እግዚአብሔር
34‘ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል፣
ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።’ ”
35በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ ዐምስት ሺሕ ሰው ገደለ፤ ሰዎቹ ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር። 36ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ።
37ናሳራክ በተባለው አምላኩ ቤተ ጣዖት ገብቶ በመስገድ ላይ ሳለ፣ አድራሜሌክና ሳራሳር የተባሉ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት፤ ከዚያም አምልጠው ወደ አራራት ሸሹ። ልጁ አስራዶንም በምትኩ ነገሠ።

Currently Selected:

2 ነገሥት 19: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ