2 ነገሥት 17
17
ሆሴዕ የመጨረሻው የእስራኤል ንጉሥ
1፥3-7 ተጓ ምብ – 2ነገ 1፥9-12
1የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዘጠኝ ዓመትም ገዛ። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ክፉ ሥራው ግን ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያህል አልነበረም። 3የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ሊወጋው መጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ገበረለትም። 4የአሦር ንጉሥ ግን ሆሴዕ እንደ ከዳው ተገነዘበ፤ ምክንያቱም ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሲጎር መልክተኞች ስለላከና በየዓመቱም ያደርግ እንደ ነበረው ለአሦር ንጉሥ ስላልገበረ ነው፤ ከዚህም የተነሣ ስልምናሶር ይዞ ወህኒ ቤት አስገባው። 5የአሦርም ንጉሥ አገሩን በሙሉ ወረረ፤ ወደ ሰማርያም ገሥግሦ ሦስት ዓመት ከበባት። 6በሆሴዕ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም በምርኮ ወደ አሦር አፈለሳቸው። እነዚህም በአላሔ፣ ጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብ እንዲሁም በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።
እስራኤላውያን በኀጢአታቸው ምክንያት ተማረኩ
7እንግዲህ እስራኤላውያን ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው፣ ከግብፅ ምድር ከፈርዖን አገዛዝ ከግብፅ ንጉሥ ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ስለ በደሉት ነው፤ እንዲሁም ሌሎች አማልክትን በማምለክ፣ 8እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳድዶ ያወጣቸውን የአሕዛብንና የእስራኤልም ነገሥታት ወደ ምድሪቱ ያገቡትን አስጸያፊ ልማድ ስለ ተከተሉ ነበር።
9እስራኤላውያን በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር በስውር አደረጉ፤ ከቃፊር መጠባበቂያ ማማ አንሥቶ እስከ ተመሸገው ከተማ ባሉት መኖሪያዎቻቸው ሁሉ በሚገኙት ኰረብቶች ላይ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ። 10በእያንዳንዱ ኰረብታ ላይና በእያንዳንዱም የተንሰራፋ ዛፍ ሥር ዐምደ ጣዖትና የአሼራን ምስል ዐምዶች አቆሙ። 11እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳድዶ ያስወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉትም ሁሉ፣ በየኰረብታው ላይ ዕጣን አጤሱ፤ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጣ ክፉ ነገር አደረጉ። 12እግዚአብሔር፣ “ይህን ማድረግ አይገባችሁም”#17፥12 ዘፀ 20፥4-5 ቢላቸውም እንኳ እነርሱ ጣዖታትን አመለኩ። 13ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለ ራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።
14ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤ እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ። 15ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዝዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።
16አምላካቸው እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አልፈጸሙም፤ አቅልጠውም ሁለት የጥጃ ምስልና የአሼራን ምስል ዐምድ ሠሩ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰገዱ፤ በኣልን አመለኩ፤ 17እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።#17፥17 ወይም ልጆቻቸው ገድሎ ጥንቈላና መተት አደረጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቍጣም አነሣሡት። 18ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ የይሁዳ ነገድ ብቻ ሲቀር እስራኤልን ከፊቱ አራቀ። 19ይሁዳም ቢሆን ከእስራኤል የተቀበለውን ልማድ ተከተለ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም። 20ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ተዋቸው፤ አስጨነቃቸው፤ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸውም ድረስ በማራኪዎቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
21እስራኤልን ከዳዊት ቤት ከለየ በኋላ፣ እነርሱ የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እስራኤል እግዚአብሔርን እንዳይከተል በማሳት ትልቅ ኀጢአት እንዲሠራ አደረገ። 22እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም። 23እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል።
አሦራውያን በሰማርያ ሰፈሩ
24የአሦርም ንጉሥ ሕዝቡን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋና ከሐማት፣ ከሴፈርዋይም ከተሞች አምጥቶ በእስራኤላውያን ቦታ እንዲገቡ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነርሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ ይኖሩ ጀመር። 25በዚያ መኖር እንደ ጀመሩም እግዚአብሔርን አላመለኩም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አንበሶች ሰደደባቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን ሰብረው ገደሉ። 26ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው።
27ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በእዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ። 28ስለዚህ ከሰማርያ ማርከው ከወሰዷቸው ካህናት አንዱ ወደ ቤቴል ተመልሶ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባቸው አስተማራቸው። 29ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወገን በየሰፈረበት ከተማ የራሱን አምላክ ሠራ፤ ያንንም ቀድሞ የሰማርያ ሕዝብ በኰረብታው ላይ በሠራው ማምለኪያ እየወሰደ አቆመ። 30ከባቢሎን የመጡት ሱኮት-በኖትን፣ ከኩታ የመጡት ኔርጋልን፣ ከሐማት የመጡት አሲማትን ሠሩ፤ 31አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅ የተባሉትን አማልክት ሲሠሩ፣ ከሴፈርዋይም የመጡት ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት አማልክታቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 32እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ወገን የመጣበትን ሕዝብ ልማድ ተከትሎ፣ በየኰረብታው ባሉት ቤተ ጣዖታት የሚያገለግሉትን ካህናት ሾመ። 33በአንድ በኩል እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፣ በሌላ በኩል ግን እንደየአገራቸው ልማድ የየራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር።
34ይህንም ልማዳቸውን እስከ ዛሬ ድረስ አልተዉትም፤ እግዚአብሔርን በአግባቡ አያመልኩም፤ እንዲሁም እስራኤል ብሎ ለጠራው ለያዕቆብ ዘሮች የሰጣቸውን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞችን አይከተሉም። 35እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዝዟቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አታምልኳቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸውም፤ 36ማምለክ የሚገባችሁ ግን በታላቅ ኀይልና በተዘረጋች ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። ለእርሱ ስገዱ፤ ለእርሱም መሥዋዕት አቅርቡ። 37የጻፈላችሁን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ምንጊዜም ተግታችሁ ጠብቁ። ሌሎች አማልክትን አታምልኩ። 38ከእናንተ ጋር የገባሁትን ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትም አታምልኩ። 39ይልቅስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እርሱ ነውና።”
40ነገር ግን በቀደመው ልማዳቸው ጸኑ እንጂ አልተመለሱም። 41እነዚህ ሕዝቦች ምንም እንኳ በአንድ ወገን እግዚአብሔርን ቢያመልኩትም፣ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው ያደረጉትን ዛሬም እንደ ቀጠሉበት ነው።
Currently Selected:
2 ነገሥት 17: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.