2 ነገሥት 15
15
የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ
1፥1-7 ተጓ ምብ – 2ዜና 26፥3-4፤ 26፥21-23
1የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ ሰባተኛው፣ ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ። 2በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ዐምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3እርሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 4ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
5 እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፤ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጽ#15፥5 የዕብራይስጡ ቃል፣ ቈዳን የሚያጠቁትን ማንኛውንም ዐይነት በሽታዎችን ያመለክታል። ነበረበት፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያ ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።
6በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 7ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በምትኩ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ
8የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ስድስት ወርም ገዛ። 9አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።
10የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በዘካርያስ ላይ አሤረበት፤ በሕዝቡ#15፥10 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማምል። አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ግን፣ በኢብላም ይላሉ። ፊት አደጋ ጥሎ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ። 11በዘካርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቧል። 12በዚህም እግዚአብሔር ለኢዩ፣ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ”#15፥12 2ነገ 10፥30 ይመ። ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ።
የእስራኤል ንጉሥ ሰሎም
13የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በእስራኤል ላይ ነገሠ። በሰማርያ ተቀምጦ አንድ ወር ገዛ። 14የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ በመሄድ አደጋ ጥሎ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገደለው፤ ከዚያም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
15በሰሎም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና የጠነሰሰውም ሤራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል።
16በዚያ ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ በቲፍሳና በከተማዪቱ ነዋሪዎች ላይ ሁሉ፣ በአካባቢዋም ጭምር አደጋ ጣለ፤ ይህን ያደረገውም የከተማዪቱን በሮች ለመክፈት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነበር፤ ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰጡሮችንም ሆድ ሁሉ ቀደደ።
የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም
17የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት፣ የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያ ተቀምጦም ዐሥር ዓመት ገዛ። 18በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ በዘመኑም ሁሉ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።
19ከዚያም የአሦር ንጉሥ ፎሓ#15፥19 ቴልጌልቴልፌልሶርም ይባላል። ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺሕ መክሊት#15፥19 34 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ብር ሰጠው። 20ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም ዐምሳ፣ ዐምሳ ሰቅል#15፥20 575 ግራም ያህል ነው። ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።
21በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 22ምናሔም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ፋቂስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ፋቂስያስ
23የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በዐምሳኛው ዓመት፣ የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በሰማርያ ከተማ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። 24ፋቂስያስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም። 25ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ ዐምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋራ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።
26በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል።
የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ
27የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በዐምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በሰማርያ ከተማ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሃያ ዓመትም ገዛ። 28እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።
29በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካን፣ ያኖዋን፣ ቃዴስንና አሦርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ጭምር ያዘ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰደው። 30ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።
31በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም
15፥33-38 ተጓ ምብ – 2ዜና 2፥1-4፤ 2፥7-9
32የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ። 33በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፣ ኢየሩሳ ትባል ነበር። 34አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 35ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር ሠራ።
36በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 37በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔን ይሁዳን እንዲወጉ አደረገ። 38ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ አባቶቹ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝም በምትኩ ነገሠ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 15: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.