2 ነገሥት 1
1
የእግዚአብሔር ፍርድ በአካዝያስ ላይ
1አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። 2በዚህ ጊዜ አካዝያስ በሰማርያ ካለው እልፍኝ ሰገነቱ ላይ ሳለ፣ ከዐይነ ርግቡ ሾልኮ ወድቆ ነበርና ታመመ፤ ስለዚህ፣ “ሄዳችሁ ከዚህ ሕመም እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ” ሲል መልእክተኞች ላከ።
3የእግዚአብሔር መልአክ ግን ቴስብያዊውን ኤልያስን እንዲህ አለው፤ “ተነሥተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና፣ ‘የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱ በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን?’ ብለህ ጠይቃቸው። 4ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከተኛህበት ዐልጋ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ።’ ” ከዚያም ኤልያስ ሄደ።
5መልእክተኞቹ ወደ ንጉሡ ሲመለሱ እርሱም፣ “ለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
6እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንድ ሰው ሊገናኘን መጥቶ፣ ‘ወደ ላካችሁ ንጉሥ ተመልሳችሁ ሂዱና፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ ሰዎች የምትልከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ከተኛህበት ዐልጋ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ።” ’ ”
7ንጉሡም፣ “ለመሆኑ ሊገናኛችሁ መጥቶ እንዲህ ያላችሁ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
8እነርሱም “ሰውየው ጠጕራም፣ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር” አሉት።
ንጉሡም፣ “ዐወቅሁት፤ ቴስብያዊው ኤልያስ ነው” አላቸው።
9ከዚያም ንጉሡ አንድ የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ወታደሮቹ ጋራ ወደ ኤልያስ ላከ። የዐምሳ አለቃውም ኤልያስ ወደ ተቀመጠበት ኰረብታ ጫፍ ወጥቶ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘ና ውረድ’ ይልሃል” አለው።
10ኤልያስም መልሶ የዐምሳ አለቃውን፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ፣ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ አንተንና ዐምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ የዐምሳ አለቃውንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች።
11እንደ ገናም ንጉሡ ሌላ የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ሰዎቹ ጋራ ላከ፤ የዐምሳ አለቃውም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘አሁኑኑ ና ውረድ’ ይልሃል” አለው።
12ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ እሳት ከሰማይ ወርዳ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው፤ ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች።
13ስለዚህም ንጉሡ ሦስተኛውን የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ሰዎቹ ጋራ ላከ። ይህም ሦስተኛው የዐምሳ አለቃ ወጥቶ፣ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ እባክህ የእኔና የእነዚህ የዐምሳዎቹ አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን። 14እነሆ፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ የፊተኞቹን ሁለት ዐምሳ አለቆችና ሰዎቻቸውን ሁሉ በላች፤ አሁን ግን ሕይወቴ በፊትህ የከበረች ትሁን።”
15የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን፣ “ዐብረኸው ውረድ፤ ደግሞም አትፍራው” አለው። ስለዚህ ኤልያስ ተነሣ፤ ዐብሮትም ወደ ንጉሡ ወረደ።
16ንጉሡንም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለመሆኑ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ስለ ራስህ ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክኸው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን? ይህን በማድረግህም ከተኛህበት ዐልጋ ፈጽሞ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ’ ” ብሎ ነገረው። 17ስለዚህ አካዝያስ ኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ።
አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም#1፥17 በዕብራይስጡ ኢዮሃራም፣ ሌላው የኢዮራም አጠራር ነው። በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 18ሌላው አካዝያስ በዘመኑ ያከናወናቸውና የፈጸማቸው ሥራዎች ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፉ አይደለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.