2 ቆሮንቶስ 8
8
የልግስና አስፈላጊነት
1ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን። 2የደረሰባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም ደስታቸው ግን የላቀ ነበር፤ ድኽነታቸው ብርቱ ቢሆንም ልግስናቸው ግን የበዛ ነበር። 3እንደ ዐቅማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከዐቅማቸው በላይ በፈቃዳቸው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁ። 4እነርሱም ቅዱሳንን ለመርዳት በሚደረገው አገልግሎት ለመሳተፍ ዕድል ያገኙ ዘንድ አጥብቀው ይለምኑን ነበር። 5እኛ ከጠበቅነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ። 6ስለዚህ ቲቶ፣ በእናንተ መካከል ቀደም ሲል የጀመረውን የልግስና ሥራ ከፍጻሜ እንዲያደርስ ለምነነው ነበር። 7እናንተም በሁሉ ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በዕውቀት፣ በፍጹም ትጋትና ለእኛም ባላችሁ ፍቅር#8፥7 አንዳንድ ቅጆች ለእናንተ ባለን ፍቅር ይላሉ ልቃችሁ እንደ ተገኛችሁ፣ በዚህም የቸርነት ሥራ ልቃችሁ እንድትገኙ ዐደራ እንላችኋለን።
8ይህን የምለው ትእዛዝ ለመስጠት ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን ሌሎች ከሚያሳዩት ትጋት አንጻር የፍቅራችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው። 9የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።
10ስለዚህ ጕዳይ የምሰጣችሁ ጠቃሚ ምክር ይህ ነው፤ ባለፈው ዓመት በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤ 11አሁንም የጀመራችሁትን ተግባር በዐቅማችሁ መጠን ከፍጻሜ አድርሱት፤ ይህም ለመስጠት የነበራችሁ በጎ ፈቃድ እውን እንዲሆን ነው። 12ለመስጠት በጎ ፈቃድ ካለን ስጦታው ተቀባይነት የሚያገኘው ባለን መጠን ስንሰጥ እንጂ፣ በሌለን መጠን ለመስጠት ስንሞክር አይደለም።
13ይህን የምንለው እናንተ ተቸግራችሁ ሌሎች ይድላቸው ለማለት ሳይሆን፣ ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው። 14በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጕድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጕድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ። 15ይህም፣ “ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም”#8፥15 ዘፀ 16፥18 ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
ቲቶ ወደ ቆሮንቶስ ተላከ
16እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ 17ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የመጣው ልመናችንን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ጕጕትና በራሱ ፈቃድ በመነሣሣት ነበር። 18ከርሱም ጋራ በወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ልከነዋል። 19ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ ዐብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጧል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው። 20በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን። 21ምክንያቱም ዐላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን፣ በሰውም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው።
22ደግሞም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ ተፈትኖ ትጉ ሆኖ የተገኘውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋራ ልከነዋል፤ አሁንም በእናንተ እጅግ ከመታመኑ የተነሣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየተጋ ነው። 23ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፣ እርሱ እናንተን ለማገልገል ዐብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችንም የሚጠይቅ ቢኖር እነርሱ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። 24ስለዚህ የፍቅራችሁን እውነተኛነትና በእናንተም የምንታመነው የቱን ያህል እንደ ሆነ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ግለጡላቸው።
Currently Selected:
2 ቆሮንቶስ 8: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.