2 ዜና መዋዕል 8
8
ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች
8፥1-18 ተጓ ምብ – 1ነገ 9፥10-28
1ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ በፈጸመበት በሃያኛው ዓመት መጨረሻ፣ 2ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች አድሶ እስራኤላውያን እንዲሰፍሩባቸው አደረገ። 3ከዚያም ሰሎሞን ወደ ሐማት ሱባ ዘመተ፤ ያዛትም። 4በምድረ በዳውም ውስጥ ተድሞርንና ቀድሞ በሐማት ሠርቷቸው የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ ሠራ። 5እንዲሁም የላይኛውን ቤትሖሮንና የታችኛውን ቤትሖሮን የተመሸጉ ከተሞች አድርጎ ከቅጥሮቻቸው፣ ከበሮቻቸውና ከመዝጊያዎቻቸው ጋራ ሠራ። 6ደግሞም ባዕላትንና የሰሎሞን ዕቃ ማከማቻ ከተሞች፣ እንዲሁም ሠረገለኞችና#8፥6 ወይም ሠረገሎች ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ሁሉ፣ በአጠቃላይ በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በግዛቶቹ ሁሉ ለመሥራት የፈለጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሠራ።
7እስራኤላውያን ያልሆኑትን ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የተረፉትን ሕዝቦች ሁሉ፣ 8እስራኤላውያን ያላጠፏቸውን፣ በምድሪቱ የቀሩትን የእነዚህን ሕዝቦች ዘሮች እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚደረገው የጕልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሰሎሞን መለመላቸው፤#8፥8 ወይም ከሌቦ ሐማት ተብሎ መተርጐም ይችላል። 9ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ ይልቁንም እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አዛዦቹ፣ ሻምበሎቹ፣ የፈረሰኞችና የሠረገለኞች አዛዦቹ ነበሩ። 10ከእነዚህም ሁለት መቶ ዐምሳዎቹ የንጉሥ ሰሎሞን ሹማምት ሰዎቹን የሚቈጣጠሩ ነበሩ።
11ሰሎሞንም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ቦታ ሁሉ ቅዱስ ስለ ሆነ፣ ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤተ መንግሥት መኖር አይገባትም” በማለት የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ እርሱ ወደ ሠራላት ቤተ መንግሥት አመጣት።
12ሰሎሞንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ፊት ለፊት ባሠራው የእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ። 13ሙሴ ስለ መሥዋዕት አቀራረብ ባዘዘው መሠረት በእያንዳንዱ የበዓል ቀን ይኸውም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻና በሦስቱ የዓመት በዓላት ማለትም በቂጣ በዓል፣ በሰባቱ ሱባዔ የመከር በዓልና በዳስ በዓል ጊዜ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ። 14የአባቱን የዳዊትን ሥርዐት በመከተልም፣ ካህናቱን በየአገልግሎት ክፍላቸው ሌዋውያኑንም ምስጋናውን እንዲመሩና በየዕለቱ ሥራቸው ካህናቱን እንዲረዱ መደባቸው። ደግሞም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት፣ የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች በልዩ ልዩ በሮች ጥበቃ ላይ በየክፍላቸው መደባቸው። 15እነርሱም ንጉሡ ግምጃ ቤቱን ጨምሮ ስለ ማንኛውም ነገር ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሰጠውን ትእዛዝ አልተላለፉም ነበር።
16የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ዕለት አንሥቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው የሰሎሞን ሥራ ሁሉ ተከናወነለት፤ በዚሁ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ከፍጻሜ ደረሰ።
17ከዚያም ሰሎሞን በኤዶም ምድር የባሕር ጠረፍ ወደሚገኙት ወደ ዔጽዮንጋብርና ወደ ኤላት ሄደ። 18ኪራምም ባሕሩን በሚያውቁት በራሱ መኰንኖች የሚታዘዙ መርከቦችን ላከለት፤ እነዚህም ከሰሎሞን ሰዎች ጋራ በመሆን ወደ ኦፊር ተጓዙ፤ ከዚያም አራት መቶ ዐምሳ መክሊት#8፥18 15 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን አመጡ።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 8: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.