2 ዜና መዋዕል 6
6
1ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ 2እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።”
3መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ። 4ከዚያም እንዲህ አለ፤
“ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤ 5‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ይሠራበት ዘንድ ከማናቸውም የእስራኤል ነገድ ከተሞች አንድም አልመረጥሁም፤ ወይም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም። 6አሁን ግን ስሜ በዚያ እንዲሆን ኢየሩሳሌምን፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲገዛም ዳዊትን መርጫለሁ።’
7“አባቴ ዳዊት፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ ዐስቦ ነበር፤ 8እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ ማሰብህ መልካም አድርገሃል፤ 9ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’
10“እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሟል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። 11በዚያም እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋራ የገባው ኪዳን ያለበትን ታቦት አኑሬአለሁ።”
ሰሎሞን በምረቃው ጊዜ ያቀረበው ጸሎት
6፥12-40 ተጓ ምብ – 1ነገ 8፥22-53
6፥41-42 ተጓ ምብ – መዝ 132፥8-10
12ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ። 13ሰሎሞንም ርዝመቱ ዐምስት ክንድ፣#6፥13 2.3 ሜትር ያህል ነው። ወርዱ ዐምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ#6፥13 1.4 ሜትር ያህል ነው። የሆነ የናስ መድረክ በውጭው አደባባይ መካከል አሠርቶ ነበር፤ በመድረኩም ላይ ወጥቶ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ 14እንዲህም አለ፤
“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋራ የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤ 15ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።
16“አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት። 17እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።
18“በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋራ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! 19ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ። 20ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ። 21ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልዩበትም ጊዜ ልመናቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ከሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
22“አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ 23ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም። በደለኛውን፣ በደሉን በራሱ ላይ አድርገህ እንደ ሥራው በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ። ንጹሑም በደለኛ አለመሆኑን አስታውቅ፤ እንደ ንጽሕናውም ክፈለው።
24“ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፣ ወደ አንተ ተመልሰውም በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ በመጸለይና ልመናቸውን በማቅረብ ስምህን ቢጠሩ፣ 25ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው።
26“አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣ 27በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸውም ምድርህ ላይ ዝናብን አዝንብ።
28“በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር፣ ዋግ ወይም አረማሞ፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚከሠትበት ጊዜ ወይም ከተሞቻቸውን ጠላት በሚከብብበት ጊዜ፣ እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ 29ከሕዝብህ ማንኛውም ሰው ወይም መላው እስራኤል ጭንቀቱንና ሕመሙን ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ማንኛውንም ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ 30በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አካሄዱ ክፈለው፤ 31ይኸውም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ አንተን እንዲፈሩህና በመንገዶችህ እንዲሄዱ ነው።
32“ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ነገር ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ ባዕድ ሰው ቢኖር፣ ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ መጥተው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣ 33አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።
34“ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ቦታ ሁሉ በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ፣ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩ፣ 35ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ፍትሕንም አጐናጽፋቸው።
36“መቼም ኀጢአት የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ፣ አንተም ተቈጥተህ ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ እነርሱም ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ የጠላት ምድር ቢጋዙ፣ 37በተጋዙበት አገር ሳሉ ወደ ልቡናቸው ቢመለሱ፣ ንስሓ ቢገቡና በምርኮ ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣ 38ተማርከው በተወሰዱበት በምርኮ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹምም ነፍሳቸው ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣ 39ከማደሪያህ ከሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን ስማ፤ ፍረድላቸውም። የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል።
40“አሁንም አምላኬ ሆይ፤ በዚህ ስፍራ ወደ ቀረበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፣ ጆሮዎችህም የሚያደምጡ ይሁኑ።
41“አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ ተነሥ፣
ከኀይልህ ታቦት ጋራ ወደ ማረፊያ ቦታህ ግባ።
እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ካህናትህ ድነትን ይልበሱ፤
ቅዱሳንህም በቸርነትህ ደስ ይበላቸው።
42 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ የቀባኸውን ሰው አትተወው፤
ለባሪያህ ለዳዊት ቃል የገባህለትን ጽኑ ፍቅር ዐስብ።”
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 6: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.