2 ዜና መዋዕል 5
5
1ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው።
ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ
5፥2–6፥11 ተጓ ምብ – 1ነገ 8፥1-21
2ከዚያም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ የሰባተኛው ወር በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።
4የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜ ሌዋውያኑ ታቦቱን አነሡ፤ 5ታቦቱን፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተሸከሟቸው። 6ንጉሥ ሰሎሞንና ዐብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ ስፍር ቍጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች በታቦቱ ፊት ሠዉ።
7ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት። 8ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። 9መሎጊያዎቹ በጣም ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከቅድስት ይታዩ ነበር፤ ከቅድስት ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 10እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።
11ካህናቱም ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እዚያ የነበሩት ካህናት በምድባቸው መሠረት ባይሆንም፣ ሁሉም ራሳቸውን ቀድሰው ነበር። 12መዘምራን የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፣ አሳፍ፣ ኤማን፣ ሄማንና ኤዶታም፣ ወንዶች ልጆቻቸውና የሥጋ ዘመዶቻቸው ሁሉ ያማረ ቀጭን በፍታ ለብሰው፣ ከመሠዊያው በስተምሥራቅ በኩል ቆመው ጸናጽል ይጸነጽሉ፣ በገና ይደረድሩና መሰንቆ ይመቱ ነበር፤ እነርሱም መለከት በሚነፉ አንድ መቶ ሃያ ካህናት ታጅበው ነበር። 13መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ በመለከት፣ በጸናጽልና በሌሎች መሣሪያዎች ታጅበውም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን እያወደሱ፣
“እርሱ ቸር ነው፣
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”
እያሉ ዘመሩ።
ከዚያም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደመና ተሞላ። 14የእግዚአብሔር ክብር የአምላክን ቤተ መቅደስ ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.