2 ዜና መዋዕል 34
34
ኢዮስያስ ያደረገው ተሐድሶ
34፥1-2 ተጓ ምብ – 2ነገ 22፥1-2
34፥3-7 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥4-20
34፥8-13 ተጓ ምብ – 2ነገ 22፥3-7
1ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄደ።
3በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ፣ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ። 4በርሱም ትእዛዝ የበኣሊም መሠዊያዎችን አፈራረሱ፤ እርሱም ከበላያቸው የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎችን አደቀቀ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶችን፣ ጣዖታቱንና ምስሎቹን ሰባብሮ ከፈጫቸው በኋላ፣ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነ። 5የካህናቱን ዐጥንት በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ፤ በዚህ ዐይነትም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። 6እስከ ንፍታሌም ባሉ በምናሴ፣ በኤፍሬምና በስምዖን ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ የፈራረሱ አካባቢዎች፣ 7መሠዊያዎችንና የአሼራ ምስል ዐምዶችን አፈራረሰ፤ ጣዖታቱን እንደ ዱቄት አደቀቀ፤ በመላው እስራኤል የሚገኙትንም የዕጣን መሠዊያዎች አነካከተ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
8ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፣ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዪቱን ገዥ መዕሤያንና የጸሓፊውን የኢዮአካዝን ልጅ ኢዮአክን የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይጠግኑ ዘንድ ላካቸው።
9እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር። 10እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ። 11እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ።
12ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣ 13የጕልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ።
የሙሴ ሕግ መጽሐፍ መገኘት
34፥14-28 ተጓ ምብ – 2ነገ 22፥8-20
34፥29-32 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥1-3
14ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።
16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ 17በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።” 18ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።
19ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20ከዚያም ንጉሡ ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓብዶንን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 21“ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ትሩፋን በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።”
22ኬልቅያስና ንጉሡ ከርሱ ጋራ የላካቸው#34፥22 አንድ የዕብራይስጥ ቅጅ እንዲሁም ቩልጌትና የሱርስት ትርጕሞች በዚህ ሲስማሙ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን ከርሱ ጋራ የላካቸው የሚለውን አይጨምሩም። ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢዪቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው የከተማው ክፍል ትኖር ነበር።
23ነቢዪቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ 24‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎቹ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ። 25እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ#34፥25 ወይም ባደረጉት ነገር ሁሉ ለቍጣ ስላነሣሡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ 26እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ 27‘በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔር ፊት ራስህን ስላዋረድህ፣ ራስህን ዝቅ አድርገህ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ ስላለቀስህ፣ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። 28እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታ እና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ”
ሰዎቹም መልሷን ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።
29ከዚያም ንጉሡ ልኮ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች በአንድ ላይ ሰበሰበ። 30ንጉሡም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ፣ ካህናቱንና ሌዋውያንን ሁሉ ከልጅ እስከ ዐዋቂ አንድም ሰው ሳይቀር ይዞ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል በሙሉ በጆሯቸው እንዲሰሙት አነበበላቸው። 31ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን እንደሚከተል ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹን፣ ሥርዐቶቹን በፍጹም ልቡና በፍጹምም ነፍሱ እንደሚጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን ኪዳን እንደሚያጸና በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ።
32ከዚህ በኋላ በኢየሩሳሌምና በብንያም የሚኖረው ሁሉ በዚህ ነገር ቃል እንዲገባ አደረገ፤ የኢየሩሳሌምም ሕዝብ የአባቶቹ አምላክ ባዘዘው የአምላክ ቃል ኪዳን መሠረት ፈጸሙ።
33ኢዮስያስም አስጸያፊ ጣዖታትን ሁሉ ከመላው የእስራኤል ግዛት አስወገደ፤ በእስራኤል የነበሩትም ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ አደረገ፤ እርሱ በሕይወት እያለም የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 34: NASV
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.