2 ዜና መዋዕል 32:24-33

2 ዜና መዋዕል 32:24-33 NASV

በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታምሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም መለሰለት፤ ምልክትም ሰጠው። የሕዝቅያስ ልብ ግን ታበየ እንጂ ስለ ተደረገለት በጎ ነገር ተገቢ ምላሽ አልሰጠም፤ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በርሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ። ይሁን እንጂ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ስለ ልባቸው ትዕቢት ራሳቸውን አዋረዱ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በዘመነ መንግሥቱ አልመጣባቸውም። ሕዝቅያስ እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ከዚህ የተነሣም ለብሩ፣ ለወርቁ፣ ለከበሩት ዕንቍዎቹ፣ ለቅመማ ቅመሞቹ፣ ለጋሻዎቹና ለተለያዩ ውድ ዕቃዎቹ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ። እንደዚሁም ለእህሉ፣ ለወይን ጠጁና ለዘይቱ ማከማቻ የሚሆኑ ግምጃ ቤቶች ለተለያዩ እንስሳት በረት ለበግና ለፍየል መንጋም በረት ሠራ። እግዚአብሔር ታላቅ ብልጽግና ስለ ሰጠው፤ ብዙ የበግና የፍየል፣ የእንስሳትም መንጋ ሰበሰበ፤ ከተሞችንም ሠራ። የላይኛውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ፣ ውሃውን በቦይ ቍልቍል ወደ ምዕራቡ የዳዊት ከተማ እንዲወርድ ያደረገም ይኸው ሕዝቅያስ ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ተከናወነለት። ነገር ግን በምድሪቱ ላይ ስለ ተፈጸመው ታምራዊ ምልክት እንዲጠይቁት፣ የባቢሎን ገዦች መልእክተኞችን በላኩ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሊፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ሊያውቅ ስለ ፈለገ ተወው። በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወኑ ሌሎች ተግባራትና ቸርነቱ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ፣ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል። ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ የዳዊት ዘሮች መካነ መቃብር በሆነው ኰረብታም ተቀበረ። በሞተም ጊዜ ይሁዳ ሁሉና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ አከበሩት። ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተካ።