2 ዜና መዋዕል 32
32
ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ዛተ
32፥9-19 ተጓ ምብ – 2ነገ 18፥17-35፤ ኢሳ 36፥2-20
32፥20-21 ተጓ ምብ – 2ነገ 19፥35፤ ኢሳ 37፥36-38
1ሕዝቅያስ እንዲህ ባለ ታማኝነት ነገሮችን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ድል አድርጎ የራሱ ሊያደርጋቸው በማሰብም የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ። 2ሕዝቅያስም ሰናክሬም መምጣቱንና ኢየሩሳሌምንም ለመውጋት ማሰቡን ባወቀ ጊዜ፣ 3ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ ከሹማምቱና ከጦር አለቆቹ ጋራ ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት። 4ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት#32፥4 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስቱ ትርጕም ግን፣ ንጉሥ ይላል። መጥተው ስለ ምን ብዙ ውሃ ያገኛሉ?” በማለት ምንጮቹን ሁሉና በምድር ውስጥ ለውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ውሃ ዘጉ። 5ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር በመገንባት የዳዊትን ከተማ ድጋፍ እርከን አጠናከረ፤ እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።
6የጦር መኰንኖችንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ በከተማዪቱ በር አደባባይ ላይ በፊቱ ከሰበሰበ በኋላ፣ እንዲህ ሲል አበረታታቸው፤ 7“በርቱ፤ ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋራ ያለው ከርሱ ጋራ ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና ዐብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 8ከእነርሱ ጋራ ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋራ ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።
9ከዚህ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሰራዊቱ ሁሉ ጋራ ለኪሶን ከብቦ ሳለ፣ የሚከተለውን መልእክት በጦር መኰንኖቹ አማካይነት፣ ለሕዝቅያስና ከርሱ ጋራ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ ላከ፤
10“የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፤ በተከበበችው በኢየሩሳሌም እስከዚህ የቈያችሁት በማን ተማምናችሁ ነው? 11ሕዝቅያስ፣ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ማለቱስ በራብና በጥማት እንድትሞቱ ሊያሳስታችሁ አይደለምን? 12ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ ‘በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በላዩም መሥዋዕት አቃጥሉ’ በማለት የራሱን አምላክ የኰረብታ ላይ መስገጃ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችንስ ያስወገደ ሕዝቅያስ አይደለምን?
13“እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁምን? ታዲያ ከእነዚያ ከአሕዛብ አማልክት ምድራቸውን ከእጄ ለማዳን ችለዋልን? 14አባቶቼ ሙሉ በሙሉ ከደመሰሷቸው ከእነዚህ መንግሥታት አማልክት ሁሉ፣ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን የቻለ አምላክ የትኛው ነው? ታዲያ አምላካችሁ እንዴት ከእጄ ሊታደጋችሁ ይችላል? 15አሁንም ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ አያስታችሁም። የየትኛውም አገር ሕዝብ ወይም መንግሥት አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ መታደግ የቻለ ስለሌለ አትመኑት። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!”
16የሰናክሬም ሹማምትም በእግዚአብሔር አምላክና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17ንጉሡም እንደዚሁ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በመሳደብ፣ “የሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች አማልክት፣ ከእጄ እንዳልታደጉ ሁሉ፣ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም” ሲል በርሱ ላይ ደብዳቤ ጻፈ። 18ከዚያም በማስደንገጥና በማስፈራራት ከተማዪቱን ለመያዝ ሲሉ በቅጥሩ ላይ ወደ ተቀመጠው ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በዕብራይስጥ ጮኹ፤ 19የሰው እጅ በሠራቸው በሌሎች የምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደ ተናገሩት ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ።
20ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ስለዚህ ጕዳይ በጸሎት ወደ ሰማይ ጮኹ። 21እግዚአብሔርም መልአክ ልኮ በአሦር ንጉሥ ሰፈር ተዋጊዎችን፣ መሪዎችንና የጦር መኰንኖችን እንዲያጠፋቸው አደረገ። ስለዚህ ንጉሡ በውርደት ወደ ገዛ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩ ቤተ ጣዖት እንደ ገባም፣ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።
22 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬምና ከሌሎችም እጅ ሁሉ አዳናቸው፤ በዙሪያቸው ካሉትም ሁሉ ጠበቃቸው#32፥22 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል የሰብዓ ሊቃናት የቩልጌት ቅጆች ግን አሳረፋቸው ይላል።፤ 23ብዙዎችም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ውድ የሆኑ ገጸ በረከቶችን አመጡለት፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።
የሕዝቅያስ ዕብሪት፣ ያከናወናቸው ተግባሮችና ሞቱ
32፥24-33 ተጓ ምብ – 2ነገ 20፥1-21፤ ኢሳ 37፥21-38፤ 38፥1-8
24በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታምሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም መለሰለት፤ ምልክትም ሰጠው። 25የሕዝቅያስ ልብ ግን ታበየ እንጂ ስለ ተደረገለት በጎ ነገር ተገቢ ምላሽ አልሰጠም፤ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በርሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ። 26ይሁን እንጂ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ስለ ልባቸው ትዕቢት ራሳቸውን አዋረዱ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በዘመነ መንግሥቱ አልመጣባቸውም።
27ሕዝቅያስ እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ከዚህ የተነሣም ለብሩ፣ ለወርቁ፣ ለከበሩት ዕንቍዎቹ፣ ለቅመማ ቅመሞቹ፣ ለጋሻዎቹና ለተለያዩ ውድ ዕቃዎቹ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ። 28እንደዚሁም ለእህሉ፣ ለወይን ጠጁና ለዘይቱ ማከማቻ የሚሆኑ ግምጃ ቤቶች ለተለያዩ እንስሳት በረት ለበግና ለፍየል መንጋም በረት ሠራ። 29እግዚአብሔር ታላቅ ብልጽግና ስለ ሰጠው፤ ብዙ የበግና የፍየል፣ የእንስሳትም መንጋ ሰበሰበ፤ ከተሞችንም ሠራ።
30የላይኛውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ፣ ውሃውን በቦይ ቍልቍል ወደ ምዕራቡ የዳዊት ከተማ እንዲወርድ ያደረገም ይኸው ሕዝቅያስ ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ተከናወነለት። 31ነገር ግን በምድሪቱ ላይ ስለ ተፈጸመው ታምራዊ ምልክት እንዲጠይቁት፣ የባቢሎን ገዦች መልእክተኞችን በላኩ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሊፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ሊያውቅ ስለ ፈለገ ተወው።
32በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወኑ ሌሎች ተግባራትና ቸርነቱ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ፣ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል። 33ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ የዳዊት ዘሮች መካነ መቃብር በሆነው ኰረብታም ተቀበረ። በሞተም ጊዜ ይሁዳ ሁሉና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ አከበሩት። ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተካ።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 32: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.