2 ዜና መዋዕል 25
25
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
25፥1-4 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥1-6
25፥11-12 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥7
25፥17-28 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥8-20
1አሜስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ አልነበረም። 3መንግሥቱም ከጸናለት በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው። 4እግዚአብሔር በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው ሕግ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች በልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ኀጢአት አይገደሉ”#25፥4 ዘዳ 24፥16 ብሎ ባዘዘው መሠረት አደረገ እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም።
5አሜስያስ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰብስቦ፣ እንደየቤተ ሰቡ በሻለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል በመላው ይሁዳና በብንያም መደባቸው። ከዚያም ዕድሜያቸው ሃያና ከሃያ በላይ የሆናቸውን ሰብስቦ፣ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ ሆነው ጋሻና ጦር መያዝ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺሕ ሰዎች አገኘ። 6እንዲሁም በመቶ መክሊት#25፥6 በዚህና በቍጥር 9 ላይ 3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ጥሬ ብር አንድ መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ከእስራኤል ቀጠረ።
7ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤልም ሆነ ከማናቸውም የኤፍሬም ሕዝብ ጋራ አይደለምና፣ እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ከአንተ ጋራ አይዝመቱ። 8ሄደህ፣ ጦርነቱን በቈራጥነት ብትዋጋም እንኳ፣ የመርዳትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።”
9አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “ታዲያ ለእነዚህ ለእስራኤል ወታደሮች የከፈልሁት መቶ መክሊት እንዴት ይሁን?” ሲል ጠየቀው።
የእግዚአብሔርም ሰው፣ “እግዚአብሔር ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።
10ስለዚህ አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እርሱ የመጡትን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው አሰናበታቸው። እነርሱም በይሁዳ ላይ ክፉኛ ተበሳጭተው ነበርና በታላቅ ቍጣ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ተመለሱ።
11አሜስያስም ኀይሉን በሚገባ አደራጅቶ ሰራዊቱን ወደ ጨው ሸለቆ መራ፤ በዚያም ዐሥር ሺሕ የሴይር ወታደሮችን ገደለ። 12የይሁዳ ሰራዊት ሌሎች ዐሥር ሺሕ ሰዎች ማረኩ፤ ወደ አንድ ዐለት ዐናት ላይም አውጥተው ቍልቍል ለቀቋቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ።
13በዚያ ጊዜ አሜስያስ ያሰናበታቸውና በጦርነቱ እንዳይካፈሉ የከለከላቸው ወታደሮች፤ ከሰማርያ እስከ ቤትሖሮን ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ ሦስት ሺሕ ሰው ገደሉ፤ እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።
14አሜስያስም ኤዶማያውያንን ደምስሶ በተመለሰ ጊዜ፣ የሴይርን ሕዝብ አማልክት ይዞ መጣ፤ ለራሱም አማልክት አድርጎ በማቆም ሰገደላቸው፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው። 15የእግዚአብሔርም ቍጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይንም ላከበት፤ ነቢዩም፣ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ ማዳን ያልቻሉትን የአሕዛብን አማልክት ርዳታ የጠየቅኸው ለምንድን ነው?” አለው።
16እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመንሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው።
ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ አምላክ ሊያጠፋህ እንደ ወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።
17የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ አማካሪዎቹን ካማከረ በኋላ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ኢዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል ላከበት።
18የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ ሚስት እንድትሆነው ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው። 19እነሆ፤ ኤዶምን አሸንፌአለሁ ብለህ ልብህ በትዕቢት ተወጥሯል፤ አሁን ክብርህን ጠብቀህ ዐርፈህ በቤትህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ለማምጣት ችግር የምትፈጥረው ለምንድን ነው?”
20የኤዶምን አማልክት ማምለክ በመፈለጋቸው፣ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኗልና፣ አሜስያስ አልሰማም። 21ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ አደጋ ጣለ። እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተጋጠሙ። 22ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 23የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ከኤፍሬም በር እስከ ማእዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ#25፥23 ዕብራይስጡ፣ 180 ሜትር ያህል ነው ይላል። ያህል ርዝመት ያለውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ። 24እርሱም በአቢዳራ ጥበቃ ሥር የነበረውንና በአምላክ ቤተ መቅደስ የተገኘውን ወርቅ፣ ጥሬ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ ከቤተ መንግሥቱም ንብረትና በመያዣ ከያዛቸው ሰዎች ጭምር ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
25የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስም፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ ዐምስት ዓመት ኖረ። 26በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነው ሌላው ተግባር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27አሜስያስ እግዚአብሔርን መከተል ከተወ በኋላ፣ አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሤራ ስለ ጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ለኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩ፤ እነርሱም ገደሉት። 28አስከሬኑን በፈረስ ጭነው አመጡ። እንደ አባቶቹም በይሁዳ ከተማ#25፥28 በጥቂት የዕብራይስጥ ቅጆች የሰብዓ ሊቃናት፣ የቩልጌትና የሱርስቱ ትርጕም (2ነገ 14፥20) ዳዊት ይላሉ። ተቀበረ።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 25: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.