2 ዜና መዋዕል 23
23
1በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፤ የመቶ አለቆች ከሆኑት ከይሮሐም ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከይሆሐናን ልጅ ከይስማኤል፣ ከዖቤድ ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከዓዳያ ልጅ ከማዕሤያ፣ ከዝክሪ ልጅ ከኤሊሳፋጥ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ። 2እነርሱም ወደ መላው ይሁዳ ሄደው፣ ሌዋውያንንና የእስራኤል ቤት አለቆችን ከየከተማው ሁሉ ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜም፣ 3ጉባኤው ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከንጉሡ ጋራ ቃል ኪዳን አደረጉ።
ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለዳዊት ዘር በሰጠው ተስፋ መሠረት እነሆ፤ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4እንግዲህ እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ዕለት ተረኛ ከሆናችሁት ከእናንተ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ አንድ ሦስተኛው በሮቹን ጠብቁ፤ 5አንድ ሦስተኛው ቤተ መንግሥቱን፣ አንድ ሦስተኛው ‘የመሠረት ቅጽር በር’ የተባለውን ጠብቁ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ይሁኑ። 6ተረኛ ከሆኑት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይግባ፤ እነርሱ የተቀደሱ ስለ ሆኑ ይግቡ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ ግን፣ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይጠብቁ#23፥6 ወይም አይግባ የሚለውን የእግዚአብሔር ትእዛዝ ይጠብቁ። 7ሌዋውያኑም እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ ይዞ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባ ማንም ሰው ይገደል፤ ንጉሡ በሚሄድበትም ቦታ ሁሉ ዐብራችሁት ሁኑ።”
8ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ ከጥበቃ ክፍሎች የትኛውንም አላሰናበተም ነበርና፣ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሥራ ላይ የሚሰማሩትንና ከሥራ የሚወጡትን የራሱን ሰዎች ወሰደ፤ 9ካህኑ ዮዳሄ በአምላክ ቤተ መቅደስ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮች፣ ትላልቅና ትናንሽ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 10ሰዎቹንም ሁሉ እያንዳንዱ መሣሪያውን በእጁ ይዞ ከቤተ መቅደሱ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ።
11ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹ የንጉሡን ልጅ አምጥተው ዘውድ ጫኑለት፤ ኪዳኑንም ሰጥተው አነገሡት፤ ቀብተውም፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” እያሉ ጮኹ።
12ጎቶልያም የሚሯሯጠውንና ደስታውን ለንጉሡ የሚገልጠውን የሕዝቡን ጩኸት ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች። 13እነሆ፤ ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዐምዱ አጠገብ ቆሞ አየች፣ የጦር መኰንኖችና መለከት ነፊዎችም በንጉሡ አጠገቡ ነበሩ፤ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ ታጅበው የበዓሉን ዝማሬ ይመሩ ነበር፤ ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ “ይህ ክሕደት ነው! ይህ ክሕደት ነው!” ብላ ጮኸች።
14ካህኑ ዮዳሄም የወታደሮች አዛዥ ወደሆኑት ወደ መቶ አለቆቹ፣ “በሰልፉ መካከል አውጥታችሁ አምጧት#23፥14 ወይም ከቅጥሩ ውስጥ አውጥታችሁ አምጧት፤ የሚከተላት ካለም በሰይፍ ግደሉት” ሲል ላከባቸው። ካህኑም፣ “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አትግደሏት” ብሎ ነበርና። 15እርሷም በቤተ መንግሥቱ ግቢ የፈረስ መግቢያ በር ወደተባለው ቦታ እንደ ደረሰች ያዟት፤ በዚያም ገደሏት።
16ዮዳሄም ራሱ፣ ሕዝቡና ንጉሡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን#23፥16 ወይም በእግዚአብሔር በሕዝቡና በንጉሡ መካከል የተደረገው ቃል ኪዳን (2ነገ 11፥17) እንዲገቡ አደረገ። 17ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ሄደው የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።
18ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈውና ዳዊትም እንዳዘዘው፣ በደስታና በመዝሙር የሚቃጠለውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት ለመደባቸው ካህናትና ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ኀላፊነት ሰጣቸው። 19እንዲሁም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅጥር በሮች ላይ ጠባቆች አቆመ።
20የመቶ አለቆቹን፣ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዦችና የአገሩን ሕዝብ ሁሉ ይዞ ንጉሡን ከላይ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወደ ታች አመጣው። በላይኛውም መግቢያ በኩል ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብተው ንጉሡን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። 21መላውም የአገሩ ሕዝብ ተደሰተ፤ ጎቶልያ በሰይፍ ስለ ተገደለች ከተማዪቱ ጸጥ አለች።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 23: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.