የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ዜና መዋዕል 18

18
ሚካያ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ
18፥1-27 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥1-28
1ኢዮሣፍጥ ታላቅ ሀብትና ክብር ባገኘ ጊዜ፣ ከአክዓብ ጋራ በጋብቻ ተሳሰረ። 2ከጥቂት ዓመታት በኋላም አክዓብን ሊጐበኝ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለርሱና ዐብሮት ለነበረው ሕዝብ ብዙ በግና በሬ ዐረደ፤ ከዚያም በራሞት ገለዓድ ላይ አደጋ እንዲጥል አግባባው። 3የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ራሞት ገለዓድን ለመውጋት ዐብረኸኝ ትሄዳለህን?” ሲል ጠየቀው።
ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱ ዐብረናችሁ እንሰለፋለን” አለው። 4ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።
5ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።
6ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።
7የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ነቢይ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምን ጊዜም ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ።
ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው።
8ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።
9የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10በዚህ ጊዜ፣ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ።
11የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዝመትባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው።
13ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ።
14ወደ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ ዐልፈው ይሰጣሉና” አለው።
15ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።
16ከዚያም ሚክያስ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ።
17የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።
18ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 19እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ።
“አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ። 20ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።
እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።
21“እርሱም፣ ‘እኔ እወጣና በገዛ ነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።
እግዚአብሔርም፣ ‘ታሳስተዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ እንግዲህ ውጣና አድርግ፤’ አለው።
22“ስለዚህ እነሆ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል”።
23ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።
24ሚክያስም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።
25ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ 26ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ፣ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሏቸው” አለ።
27ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።
አክዓብ በሬማት ገለዓድ ተገደለ
18፥28-34 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥29-36
28ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ። 29የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገቡ።
30በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋራ እንዳትዋጉ” ብሎ አዝዟቸው ነበር። 31የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከርሱ መለሳቸው፤ 32የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።
33ይሁን እንጂ አንዱ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው። 34ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ እስከ ምሽት ድረስ ተደግፎ ነበር፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ሞተ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ