2 ዜና መዋዕል 14
14
1አብያ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አሳ በርሱ ፈንታ ነገሠ፤ በዘመኑም በምድሪቱ ለዐሥር ዓመት ሰላም ሆነ።
የይሁዳ ንጉሥ አሳ
14፥2-3 ተጓ ምብ – 1ነገ 15፥11-12
2አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ 3ባዕዳን መሠዊያዎችንና ማምለኪያ ኰረብቶችን አስወገደ፤ ማምለኪያ ዐምዶችን አፈረሰ፤ አሼራ ለተባለች ጣዖት አምላክ የቆሙ የዕንጨት ቅርጽ ምስሎችንም#14፥3 በሁለተኛው የዜና መዋዕል መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ አሼራ የምትባለው ጣዖት አምላክ ምስል ነው። ቈራረጠ፤ 4የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ፣ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ የይሁዳን ሕዝብ አዘዘ። 5ከእያንዳንዱም የይሁዳ ከተሞች የማምለኪያ ኰረብቶችንና የዕጣን መሠዊያዎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በርሱ አገዛዝ ዘመን ሰላም አገኘች። 6በምድሪቱ ሰላም ስለ ሰፈነ፣ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። እግዚአብሔር ዕረፍት ስለ ሰጠውም፣ በዘመኑ የተዋጋው ማንም አልነበረም።
7እርሱም ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ አላቸው፤ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ማማ፣ መዝጊያና መወርወሪያ ያላቸውን ቅጥሮች በዙሪያቸው እናብጅ። አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም የኛው ናት፤ እኛ ፈለግነው፤ እርሱም በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጠን” እነርሱም ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም።
8አሳ ታላላቅ ጋሻና ጦር የያዙ ሦስት መቶ ሺሕ የይሁዳ ሰዎች እንዲሁም ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሰማንያ ሺሕ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ።
9ኢትዮጵያዊው ዝሪ አንድ ሚሊዮን#14፥9 ዕብራይስጡ አእላፍ ወይም እልፍ ጊዜ እልፍ ይላል። ሰራዊትና ሦስት መቶ ሠረገላ ይዞ በመውጣት እስከ መሪሳ ድረስ መጣባቸው። 10አሳም ሊገጥመው ወጣ፤ መሪሳ አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆም የውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።
11በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ደካሞችን ከኀይለኞች የሚታደግ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።”
12 እግዚአብሔርም ኢትዮጵያውያንን በአሳና በይሁዳ ፊት መታቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ሸሹ፤ 13አሳና ሰራዊቱም እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዷቸው፤ እጅግ ብዙ ቍጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስለ ወደቁም፣ ሊያንሰራሩ አልቻሉም፤ በእግዚአብሔር ፊትና በሰራዊቱ ፊት ተደመሰሱ። የይሁዳም ሰዎች እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ። 14በጌራራ ዙሪያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ወደቀባቸው ከተሞቹን ሁሉ አጠፏቸው፤ እጅግ ብዙ ምርኮም በዚያ ስለ ነበር፣ በዘበዟቸው። 15እንዲሁም በእረኞች ሰፈር ላይ አደጋ ጥለው እጅግ ብዙ በጎች፣ ፍየሎችና ግመሎች ማረኩ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 14: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.