የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ዜና መዋዕል 12

12
ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ
12፥9-16 ተጓ ምብ – 1ነገ 14፥2114፥25-31
1ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ፣ እርሱና እስራኤል#12፥1 በዜና መዋዕል ካልዕ መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ ይሁዳ ነው። ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። 2እግዚአብሔርን ካለመታመናቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። 3ከግብጽ ዐብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺሕ ፈረሰኞችና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የሊቢያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣ 4የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቍጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ።
5ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ ይሁዳ መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።
6የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ።
7 እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም። 8ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለርሱ ይገዛሉ።”
9የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ሁሉንም ነገር አጋዘ። 10ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ። 11ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር።
12ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ ከርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም። በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር።
13ንጉሥ ሮብዓም በሚገባ ተደላድሎ በኢየሩሳሌም በንጉሥነቱ ቀጠለ፣ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም፣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። 14እግዚአብሔርን ይሻ ዘንድ ልቡን ስላላዘጋጀ ክፉ ነገር አደረገ።
15ሮብዓም በዘመነ መንግሥቱ ያከናወናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ነቢዩ ሸማያ በጻፈው የታሪክ መዝገብና ባለራእዩ አዶ በዘገበው የትውልድ ሐረግ ታሪክ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። 16ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ አብያም በርሱ ፈንታ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ